ፈሳሹ ገመድ

አፍሪካ ካላት አጠቃላይ የሃይድሮ ኤሌክትሪክ አመንጪ የውሃ ሀብት 8 በመቶውን ብቻ ጥቅም ላይ እንዳዋለች መረጃዎች ያመላክታሉ

ውሃ ሕይወት ከሆነ ወንዞች የደም ቧንቧዎች ናቸው፤ ይላል የዓለም ግድቦች ኮሚሽን ግድብና ልማት (DAMS AND DEVELOPMENT) በሚል ርዕስ እ.ኤ.አ 2017 ይፋ ባደረገው መረጃ፡፡

ዋና መቀመጫውን በቱርክዬ አንካራ ከተማ ያደረገው የውሃ ፖሊሲ ማህበር እ.ኤ.አ በጥር 29 ቀን 2014 ከሁሉም ጎረቤቶቿ ጋር የውሃ ድንበር ያላት ሀገር (A country with water borders with all neighbours) በሚል ርዕስ ይፋ ባደረገው መረጃ መሰረትም ቱርክዬን ጨምሮ 150 የዓለማችን ሀገራት ውሃ ድንበራቸው ነው፤ ከጎረቤቶቻቸው ጋር የሚተሳሰሩበት ፈሳሽ ገመድ፡፡

እንደ መረጃው ከሆነ ውሃ የ21ኛውን መቶ ክፍለ ዘመን ፖለቲካዊ እና ኢኮኖሚያዊ ሁኔታ በመቅረጽ ረገድ ትልቅ ሚና አለው፡፡ በተለይም በዓለማችን የኢንዱስትሪ አብዮት በዋነኛነት በ18ኛው እና በ19ኛው መቶ ክፍለ ዘመን መገባደጃ ላይ ህብረተሰቡን ከግብርና ወደ ኢንዱስትሪ ያሸጋገረ ጉልህ የቴክኖሎጂ እና የማህበራዊ ለውጥ ወቅት እንደነበር የታሪክ ድርሳናት ምስክር ናቸው፡፡

ይሁን እንጂ በወቅቱ የተተገበረው ያልተገደበ የእድገት ሞዴል፣ የውሃ ሃብት መበከል፣ የፍጆታ መጨመር፣ ፍትሐዊ ያልሆነ የውሃ ስርጭት በጊዜ እና በቦታ መባባሱ፣ በፍጥነት እየጨመረ እና የአየር ንብረት መዛባትን እያባባሰው በመምጣቱ የውሃ አስተዳደርን  ጉዳይ በዓለም አቀፍ አጀንዳዎች ውስጥ ግንባር ቀደም አድርጎታል ይላል የውሃ ፖሊሲ ማህበር መረጃ።

ከዓለም 60 በመቶ የሚሆነው የገጸ ምድር የውሃ ሃብት፣ 40 በመቶ የሚሆነው የዓለም ህዝብ በሚገኝባቸው ተፋሰስ ውስጥ የሚገኝ ነው፡፡ ይህም የጋራ ሃብቶችን በመምራት ረገድ በፍትሐዊነት ላይ የተመሰረተ ትብብር እንደሚያስፈልግ ያሳያል ይላል መረጃው።

በዓለማችን የወንዞች አሊያም የውሃ ጉዳይ አስተሳሳሪም፣ አከራካሪም አንዳንዴም ጦር የሚያማዝዝ ነው። በመሆኑ ቀላል የማይባሉ ሀገራት በዓለም አቀፍ መንግስታት ዘንድ የተቀመጡ ስምምነቶች እንደተጠበቁ ሆኖ በሰጥቶ መቀበል መርህ  ድንበር ተሻጋሪ የውሃ ሀብቶቻቸውን በጋራ የሚጠቀሙበትን አሰራር ዘርግተዋል፡፡

ወንዞችን አልምቶ በጋራ መጠቀም በሚል ርዕስ የጀርመን ልማት ተቋም (German Development Institute) እ.ኤ.አ በ2024  ይፋ ባደረገው መረጃ መሰረት  በዓለማችን ብራዚልን የመሳሰሉ ሀገራት ድንበር ተሻጋሪ ወንዞቻቸውን በጋራ አልምተው በመጠቀም ላይ ናቸው፡፡

በወሰን ተሻጋሪ የውሃ ሀብት አያያዝ ላይ መንግስታት መተባበር አለባቸው የሚለው መረጃው፣ በተለይ ለአየር ንብረት ለውጥ ተጽእኖ ተጋላጭ በሆኑ አካባቢዎች እና የውሃ እጥረት ባለባቸው ቀጣናዎች የበለጠ ትብብር አስፈላጊ ነው። ድንበር ተሻጋሪ ተፋሰሶች እና የውሃ ማጠራቀሚያዎች በድንበር አካባቢ በሚኖሩ ማህበረሰቦች መካከል ኢኮኖሚያዊ እና ማህበራዊ ትስስር ይፈጥራሉ።

እንደ መረጃው ከሆነ ግብርና፣ ኢንዱስትሪ፣ ኢነርጂ እና የውሃ አቅርቦት እና ንፅህናን የመሳሰሉ በውሃ ሀብት ላይ የተመሰረቱ ፕሮጀክቶችን በሚገባ ለመተግበር ሀገራት በላቀ ደረጃ መተባበር አለባቸው።

እንደ የዓለም ግድቦች ኮሚሽን (The World Commission on Dams) መረጃ ከሆነ ደግሞ ከዓለማችን በውሃ ከበለጸጉ ሀገራት መካከል ብራዚል፣ ሩሲያ፣ ካናዳ እና አሜሪካ  በቀዳሚነት ይጠቀሳሉ፡፡ እነዚህ ሀገራት ወንዞችን፣ ሐይቆችን እና የከርሰ ምድር ውሃን ጨምሮ ከፍተኛ መጠን ያለው የንፁህ ውሃ ሃብት አላቸው።

ታዲያ ቀላል የማይባሉ የዓለማችን ሀገራት የውሃ ሀብታቸውን በጋራ በማልማት ከፍ ከፍ ማለታቸውም በመረጃው ተመላክቷል፡፡ ለአብነትም በብራዚል እና በፓራጓይ አብሮ የማደግ እሳቤ በጥምረት የሰሩት የ‘ኢታይፑ’ ግድብ አንዱ ነው፡፡ ግድቡ የሁለቱን ሀገራት ድንበር የሚያጠቃልል ትልቅ የውሃ ኃይል ማመንጫም ነው።

የ‘ኢታይፑ’ ግድብ በዓለማችን ትልቁ የሃይድሮ ኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ነው። ግድቡ በ‘ፓራና’ ወንዝ ላይ የሚገኝ ሲሆን፣ በብራዚል እና በፓራጓይ መካከል ያለውን ድንበር ያካልላል፡፡ ግድቡ ለሁለቱም ሀገራት ትልቅ የኤሌክትሪክ ኃይል ምንጭ ሲሆን ከአጠቃላይ የኤሌክትሪክ ፍላጎታቸው ከፍተኛውን ድርሻም ይይዛል።

በብራዚል እና በፓራጓይ የጋራ ስምምነት የተገነባው ይህ የ‘ኢታይፑ’ ግድብ  እ.ኤ.አ በ 1975 ግንባታው የተጀመረ ሲሆን፣ በ1984 ወደ አገልግሎት ገብቷል። ግድቡ 14 ሺህ  ሜጋ ዋት የማመንጨት  አቅም አለው፡፡ በተለይም በዓመት ከ75 ቴራዋት-ሰዓት በላይ የኤሌክትሪክ ኃይል ያመርታል። ይህ ኃይል ለሁለቱ ሀገራት እኩል ይከፋፈላል፡፡ ታዲያ ፓራጓይ – አነስተኛ የህዝብ ብዛት እና አነስተኛ የኃይል ፍላጎት ያላት በመሆኑ አብዛኛውን ድርሻዋን መልሳ ለብራዚል ትሸጠዋለች፡፡

ሳልቶ ግራንዴ ግድብን ደግሞ ሁለቱ የደቡብ አሜሪካ ሀገራት አርጀንቲና እና ኡራጓይ በጋራ ያስተዳድሩታል፡፡ ይህ ግድብ 1 ሺህ 890 ሜጋ ዋት ሀይል የማመንጨት አቅም አለው፡፡ ይህንንም ሁለቱ ሀገራት እኩል ይካፈሉታል። ግድቡን በጋራ አልምተው መጠቀም በመቻላቸው በነዳጅ ላይ የነበራቸውን ጥገኝነትም ለመቀነስ ረድቷቸዋል፡፡

ውሃ በምድር ላይ ካሉት በጣም አስፈላጊ እና ኃይለኛ ንጥረ ነገሮች አንዱ ነው። ጥማትን ከማርካት፣ ሰብሎችን መመገብ እና ስነ-ምህዳሮችን ከመደገፍ ባለፈ ውሃ መልክዓ ምድርን የመቅረጽ፣ የኤሌክትሪክ ኃይል የማመንጨት እና ኢኮኖሚን መዳኘት​​ የሚችል ታላቅ የተፈጥሮ ሀብት ነው፡፡

ውሃ በርግጥም ሕይወት ነው። ደግሞም በአግባቡ ካልተያዘ ህይወትን ሊወስደውም ይችላል። ይህንን ኃይል በጥበብ ማስተዳደር ከሰው ልጆች ቀጣይ ፈተናዎች መካከል  አንዱ እንደሆነም የዓለም ግድቦች ኮሚሽን መረጃ ያመለክታል።

በዓለም አቀፍ ኢነርጂ ኤጀንሲ (IEA 2010፣ 2011) በታተመ መረጃ መሰረት፣ 33 በመቶ የሚሆነው የዓለም የውሃ ሀብት ብቻ ጥቅም ላይ እየዋለ ነው፡፡ አፍሪካ ደግሞ ከአጠቃላይ የማመንጨት አቅሟ 7 ወይም 8 በመቶውን ብቻ ጥቅም ላይ አውላለች፡፡

ወንዞችን፣ ሐይቆችን እና የከርሰ ምድር ውሃ ሀብቶችን በሚጋሩ ጎረቤት ሀገራት መካከል ሰላማዊ ትብብር እና ዘላቂ ልማት ለመፍጠር የወሰን ተሻጋሪ የውሃ ሃብት አስተዳደር ጽንሰ ሃሳብን መተግበር ወሳኝ ነው። ይሁን እንጂ እነዚህ ሀብቶች በጥንቃቄ ካልተያዙ በተለይ ሀገሮች ከጋራ ዓላማ ይልቅ ለአንድ ወገን ጥቅም ሲያስቀድሙ የግጭት ምንጭ ሊሆኑ ይችላሉ።

በሌላ በኩል ደግሞ አብሮ መለወጥን ያስቀደሙ ሀገራት ወንዞቻቸውን ወይም የውሃ ሀብቶቻቸውን በጋራ በማልማት ከፍ ከፍ እያሉ ነው፡፡ ለአብነትም በመካከለኛው እና በምስራቅ አውሮፓ የሚገኘው የ‘ዳኑቤ’ ወንዝ፣ ህንድና ፓኪስታን የሚጋሩት፣ የ‘ኢንዱስ’ ወንዝ በደቡብ አሜሪካ የሚገኘው እና አርጀንቲና፣ ቦሊቪያ፣ ብራዚል፣ ፓራጓይ እና ኡራጓይ የሚጋሩት የ‘ላፕላታ’ ተፋሰስን መጥቀስ እንችላለን፡፡

በርግጥም  ሀገራት የውሃ ሀብትን በፍትሐዊነት አልምቶ መጠቀም እና በሰጥቶ መቀበል መርህ ከጎረቤቶቻቸው ጋር አብሮ ለማደግ ከወሰኑ፣ ሰላም እና መረጋጋትን፣ ዘላቂ ልማትን፣ የአካባቢ ስነ ምህዳር መጠበቅን፣ በጎርፍና ተያያዥ ችግሮች የሚመጡ የተፈጥሮ አደጋዎችን መከላከልን፣ እየተደጋገመ የሚመጣ ድርቅን ማስቀረትን እንዲሁም በንግድና ትራንስፖርት ትስስር ሊመጡ የሚችሉ ዘርፈ ብዙ ጥቅሞችን እንደሚያገኙ የዓለም ግድቦች ኮሚሽን፣ ግድብና ልማት (DAMS AND DEVELOPMENT) በሚል ርዕስ እ.ኤ.አ 2017 ይፋ ባደረገው መረጃ ላይ ሰፍሯል፡፡

በመለሰ ተሰጋ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review