ፈጠራን የቀሰቀሱ ፈጠራዎች

You are currently viewing ፈጠራን የቀሰቀሱ ፈጠራዎች

ኪነ ጥበብ በሰው ልጆች ህይወት፣ ማንነት፣ አኗኗርና የእለት ተእለት መስተጋብር ውስጥ ትልቅ ድርሻ አለው። ኪነ ጥበብ አብሮነትን ያንጸባርቃል። ታሪክን ይዘክራል፡፡ ባህልን ይገልጻል። የአንድን ማህበረሰብ ወግ እና አጠቃላይ ኑረት በውስን ቃላትና ፈጠራ ያንጸባርቃል፡፡ ሥነ ምግባርን ይቀርጻል። መከባበርን ያጸናል፡፡ ከድባቴ ያወጣል። ከሃዘን ያጽናናል፡፡ የሀገር ፍቅርን ከፍ ያደርጋል፡፡

አለፍ ሲልም በፈጠራ የተሞላው ጥበብ ራሱ የፈጠራ ምንጭ ይሆናል፡፡ በዓለም ላይም በፊልምና በልብ ወለድ ምናብ ከተንጸባረቁ በኋላ ወደ ተጨባጭ ቁስ የተቀየሩ የፈጠራ ስራዎች እጅግ በርካታ ናቸው፡፡ ኪነ ጥበብን መነሻ አድርገው የተሰሩ መኪናዎች፣ አውሮፕላኖች፣ የቤት ዲዛይኖች፣ የአለባበስ ዘይቤዎች፣ አመጋገብ እና በርካታ ቴክኖሎጂዎች ይገኛሉ፡፡

ለአብነትም ከሰሞኑ በቻይና በምድር በሰማይም እንዲሁም በውሃ ጥቅም ላይ የሚውል ፈጠራ መሰራቱን ተከትሎ በርካቶች የይስማዕከ ወርቁን “ዴርቶጋዳ” መጽሐፍ ያስታውሳሉ። በዚህ መጽሐፍ ውስጥ የተገለጸችው ዴር 33 በሳይንቲስት ሻጊዝ የተነደፈች በዴርቶጋዳ ጥበበኞች ህልውና ያገኘች፤ እንደ መኪና በየብስ እንደ አሞራ በሰማይ የምትበር የተራቀቀች የዴርቶጋዳ ውጤት ናት። ዴር 33 የዴርቶጋዳ አባላት ራዕይ ተምሳሌት ናት።

የሥነ ጽሑፍ ሃያሲው መስፍን ማሞ ጉዳዩን አስመልክተው ኢትዮ ሪፈርንስ በተሰኘ ገጸ-ድር ላይ እንዳሰፈሩት ሳይንቲስት ሻጊዝ ሞቷል፤ ዓርማው ግን አልወደቀም። በዶ/ር ሚራዥ፤ በሞሳዷ ሲራጳ፤ በአሜሪካ አየር ሀይል ውስጥ ዝነኛ አብራሪ በነበረው ጌራ፤ በቁጥር ሁለት የዴርቶጋዳ ኢትዮጵያውያን ሳይንቲስቶችና ምሁራን፤ በዴር 33 ራዕዩ ዛሬም አለ። እነዚህ ሁሉና በዚህ ቅኝት ያላነሳናቸው  የዴርቶጋዳ ገፀ ባህርያት  በታሪኩ ውስጥ ባላቸው ሚና እና ሰብዕና ዕውቀትና ተልዕኮ አንባቢን በስሜት ማዕበል እያናጡ፤ በታሪኩ መርከብ እያንሳፈፉ፤ ከምዕራፍ  ምዕራፍ  እሚያስፈነጠሩ ናቸው፡፡

ዴር 33 የዴርቶጋዳ አባላት ራዕይ ተምሳሌት ናት። እስካዛሬ በተሳካ ሁኔታ ወደ እውን ዓለም ያልተቀየረች፣ መጽሐፉ ከተጻፈ በኋላ ግን በተለያየ ሀገራት እየተሞከረች ነው፡፡ ይህ የሚያሳየው ኪነ ጥበብ ለፈጠራ ስራዎች እንደ መነሻ እንደሚያገለገል ነው፡፡

ማሎሪ ሾትዌል የተሰኙ የዘርፉ ተመራማሪ በበኩላቸው “How Art Makes Us More Human: Why Being Creative is So Important in Life” በሚል ርዕስ አንድ ጽሑፍ ለንባብ አብቅተዋል፡፡ “ካልቲቬት አርት ኤንድ ኢጁኬሽን” በተሰኘ ገጸ-ድር ላይ  እ.ኤ.አ. 2023 ባሰፈሩት ጽሑፍ ጥበብ በትምህርት እና በህይወት ውስጥ ትልቅ ሚና ይጫወታል። ምክንያቱም የፈጠራ አስተሳሰብን የሚያበረታታ፣ ሰዎች ስሜታቸውን እና ሀሳባቸውን የሚገልጹበት መድረክ ነው። በተጨማሪም የኪነ ጥበብ ምስላዊ ውክልና ልጆችም ሆነ ማንኛወም ሰው መረጃን የመተንተን፣ የመከራከሪያ ነጥብ መፍጠር፣ በቴክኖሎጂ የታገዙ ፈጠራዎችን የመሞከር እና የመሳሰሉ ክህሎቶችን እንዲያዳብሩ ይረዳቸዋል ይላሉ።

በእርግጥም ጥበብ እና ፈጠራ ሁል ጊዜ ቀጥተኛ ግንኙነት አላቸው፡፡ ተመሳሳይ ነገሮችን ይጋራሉ፡፡ ምናባዊ አቅምን ወደ ተጨባጭ ነገር ወደመቀየርም ያተኩራሉ። ከዳቪንቺ የራዕይ ንድፈ ሃሳቦች  እስከ ዘመናዊው  ሰው ሰራሽ አስውሎት  የጥበብ፣ ፈጠራ እና የቴክኖሎጂ ግንኙነት የተያያዘ ሆኖ ይስተዋላል፡፡

ራንጃን ፓትሮ የተሰኙ ሌላ ጸሐፊ በበኩላቸው፤ “The Role of Art in Fostering Innovation” በሚል ርዕስ ባለፈው ዓመት ባጋሩት ጽሑፍ  ላይ እንደጠቀሱት  ኪነ ጥበብ የወደፊቱን ዓለም ለመረዳት ያግዛል፡፡ ሰዎች ምን አይነት ህይወት ይኖራሉ? ከተሞች ምን መልክ አላቸው? መኪናዎችና አውሮፕላኖች ምን ሊመስሉ ይችላሉ? የገንዘብ ግንኙነቱና ተግባቦቱ እንዴት ይሆናል? የሚለውን ቀድሞ ይተነብያል። በሳይንቲስቶች ህሊና ላይ ምስል ይከሰታል፡፡ ይህ ደግሞ ወደ እውነት እና ተጨባጭ ቁስ ይቀየራል፡፡

 “ጥበብ እና የቴክኖሎጂ ፈጠራ ልክ በዴርቶጋዳ መጽሐፍ ውስጥ እንደተጠቀሰው ሁሉ  የተሳሰሩ ናቸው። ለምሳሌ የቴክኖሎጂ አምራች ኩባንያዎች እና ስራ ፈጣሪዎች መነሻ ሃሳብን ከፊልሞችና ከልብ ወለዶች ይወስዳሉ፡፡ይህን ጊዜ ነው ኪነ ጥበብ ለፈጠራ እንደ መነሻ ሆነ የምንለው” ይላል በቅርቡ “የብሌን አንዳች” የተሰኘ መጽሐፍ ለንባብ ያበቃው ደራሲና ጋዜጠኛ ዋለልኝ አየለ፡፡

ዋለልኝ “በእኛ ሀገር ቴክኖሎጂው ካለማደጉ ጋር ተያይዞ እነዚህን የምእናብ ስራዎች ወደ ተጨባጭ እውነታዎች የመቀየር ስራ በስፋት አይስተዋልም። ይህ ብቻም ሳይሆን ‘ለፈጠራ የሚሆን ሳይንሳዊ ልብ ወለዶችና ፊልሞች በምን ያህል ደረጃ ይገኛሉ?’ የሚለውም መታየት አለበት፡፡ በሌሎች ሀገራት ሳይንሳዊ ፊልም እና ልብወለድ አድጓል። ሳይንቲስቶች እነዛን ምእናባዊ የፈጠራ ጥበቦች መነሻ አድርገው መኪናዎችን ይሰራሉ፡፡ ቴክኖሎጂ ይፈጥራሉ፡፡ ይህ ነገር እኛም ሀገር ቢለመድ ጥቅሙ ብዙ ነው፡፡ ኪነ ጥበቡን ከሌሎች ዘርፎች ጋር ለማስተሳሰርም እድል ይፈጥራል፡፡ ምክንያቱም መጪውን ዘመን መተንበይ የሚችሉት ደራሲዎችና የኪነ ጥበብ ሰዎች ናቸው ይላል፡፡

ከዋለልኝ ሃሳብ ጋር የሚመሳሰል ሃሳብ በ“ቻት ሴንተር ኔት” ገጸ-ድር ላይ ሰፍሮ እናገኛለን፡፡ ዘመናዊ ስልኮች እንደ አሁኑ ባልበዙበት ዘመን፣ የሰው ልጅ ጨረቃን ለመርገጥ ህልም እንኳን ሳይኖረው፣ የበይነመረብ ነገር ሩቅ በሆነበት ወቅት  ባለራዕይ አርቲስቶች እና ፀሐፊዎች ግን ይህ እንደሚሆን ቀድመው በስራቸው ተንብየዋል፡፡ ዛሬ የምንጠቀምባቸውን ቴክኖሎጂዎች የሚተነብዩ መጽሐፎችን ጽፈዋል፡፡ ፊልሞችን ሰርተዋል፡፡

ከአስደናቂ ቴክኖሎጂዎች እስከ አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ድረስ የማሰብ ችሎታ ያላቸው ቻትቦቶች ወይም ቨርቹዋል ሪያሊቲ ቪዲዮ ጌሞች እና እንደ አውቶሚክ ቦምብ ያሉ አደገኛ ግኝቶችም ጭምር ቀድመው የታዩት በፊልምና በልብ ወለዶች ውስጥ ነው። ጸሐፊዎች በምዕናብ ስለ ወደፊቱ ጊዜ አስቀድመው አይተዋል። ዛሬ በ21ኛው ክፍለ ዘመን የህይወታችን አካል የሆኑ ቴክኖሎጂዎችን እና ፈጠራዎችን የኪነ ጥበብ ውጤቶች ናቸው ብንል ማጋነን አይሆንም፡፡ እዚህ ጋር ከላይ የጠቀስነው ገጸ-ድር “5 books that predicted 21st century technologies that we use today” በሚል ካስቀመጣቸው መጽሐፍት ውስጥ የተወሰኑትን ለመጥቀስ እንሞክር፡፡

በዚህ ዘርፍ ውስጥ “ፋራናይት 451” የተሰኘው መጽሐፍ በቀዳሚነት ይጠቀሳል፡፡ በሬይ ብራድበሪ እ.ኤ.አ. በ1953 የተጻፈው ይህ ልብወለድ መጽሐፍ ከሳይንስ ልቦለድ ሥነ-ጽሑፍ ዋና ሥራዎች መካከል አንዱ ብቻ ሳይሆን፣ የቴክኖሎጂ ዘመንን በተመለከተ አስደናቂ ትንበያዎችን የያዘ ነው። በመጽሐፉ ውስጥ የብሉቱዝ ጆሮ ማዳመጫዎች ቀጥተኛ ምሳሌዎች ታይተዋል፡፡ ስክሪን ቴሌቪዥኖች በምእናብ ተስለዋል፡፡ ይህ መጽሐፍ በርካታ ቴክኖሎጂዎችን ቀድመው መተንበይ ከቻሉ ስራዎች መካከል ተጠቃሽና ዘመን አይሽሬ በመባልም የሚታወቅ ነው፡፡

“ዘ ኤጅ ኦፍ ኢንተለጀንስ” የተሰኘውና እ.ኤ.አ. በ1999 በሬይ ኩርዝዌል የተጻፈው መጽሐፍም ለፈጠራ የሚሆኑ እጅግ ጠቃሚ ትንበያዎችን ይዟል። አንዳንዶቹ አሁንም ሆነ ወደፊት ይሆናሉ ብሎ ለማሰብ አደጋች ናቸው። የቨርቹዋል መነጽሮች፣ በራሳቸው የሚሰሩ ማሽኖች ናኖ ኢንጂነሪንግ፣ ዲጂታል የርቀት ትምህርት፣ በAI ቁጥጥር የሚደረግባቸው የሰው ሰራሽ አካላት፣ አውቶማቲክ ትርጉም እና ሌሎች የግንኙነት ምስጢራትም በዚህ መጽሐፍ ውስጥ የተካተቱ ናቸው፡፡ እንዳንዶቹ ወደ ተጨባጭ እውነት እየተቀየሩ ሲሆን፤ ሌሎች ደግሞ ገና በሳይንቲስቶች ምርምር እየተደረገባቸው ነው፡፡

በእኛም ሀገር ከመሰል መጽሐፍት ውስጥ ከዴርቶጋዳ በተጨማሪ “የቢሆን ዓለም” የተሰኘ መጽሐፍ መጥቀስ ግድ ይሆናል። አውጊስቲን የተባለ ገጸ ባህሪ በሰው እጅ ህይወቱ ያልፋል፡፡ እውጊስቲን ገዳዩን በአይኑ አይቷል፡፡ ማን እንደመታውና እንደገደለው የወንጀለኛው ስም አብሮ ሲወጣ ይተነብያል፡፡

ቀጥሎም የሟቹ ማለትም የአውጊስቲን አእምሮ በቀዶ ጥገና ትግስት ፈረደ ለተባለች ገጸ ባህሪ (ለገዳዩ ፍቅረኛ) ይገጠማል። ይህም እርሷ ፍቅረኛዋን ባየች ጊዜ ልዩ ጥላቻ እንዲያድርባት እና ከተቻለም እንድትገድለው ለማድረግ የታሰበ ክፋት ነው፡፡ አእምሮዋ በሟች አእምሮ የተቀየረላት ትግስትም ፍቅረኛዋን ለመግደል ሞክራ በቁጥጥር ስር ውላለች። ስለዚህ ትግስት በአካል ራሷ፣ በአእምሮና አስተሳሰቧ ግን ሟች አውጊስቲንን ሆና ስትኖር ይተነብያል፡፡ በዚህም ፍቅረኛዋን ስታይ በጥላቻ እና በፍርሃት መጮህ ቀጠለች። ፍቅረኛዋ ግራ ይጋባል፡፡ በመጨረሻም በዚህ ተንኮል የተሳተፉት የአእምሮ ንቅለ ተከላ ዶክተር ሌላ መላ ዘየዱ፡፡ የትግስት አእምሮ ለሁለተኛ ጊዜ በሌላ ሴት አእምሮ እንዲቀየር፡፡ ይሁን እንጂ 2ኛው ንቅለ ተከላ ፍሎረንስ ከተባለች በመኪና አደጋ ከሞተች ሴት ነበር፡፡ ይሁንና ይህችም አካሏ ትግስት ይሁን እንጂ አእምሮዋ የፍሎረንስ በመሆኑ አስተሳሰቧ እርሷን መሰለ፡፡ ወደ ፍሎረንስ ቤተሰቦች ስትሄድ፣ በመኪና አደጋ የሞተችውን ፍሎረንስ ልጅ ስታሳድግ ያሳያል፡፡

ሁኔታው ሊደንቅም ሊያሳዝንም ይችላል የሚለው መጽሐፉ የአንጎል ልውውጥና ንቅለ ተከላ ለክፋት ሳይሆን የሰውን ልጅ ለመጥቀም ቢውል መልካም እንደሆነ ያሳስባል፡፡ በ1983 ዓ.ም በደራሲ ደጉ ቁምቢ የተጻፈው “የቢሆን ዓለም” ሳይንስ ነክ ልቦለድ መጽሐፍ ተጨባጭ ዓለም ሊቀየሩ የሚችሉ ፈጠራዎችን ቀድሞ የተነበየ ነው ማለት ይቻላል፡፡

ከመጽሐፍ በተጨማሪ ተጨባጭ እውነት የቀየሩ የኪነ ጥበብ ሃሳቦች እጅግ በርካታ ናቸው፡፡ ለአብነትም እ..አ.አ በ2013 የተሰራውን “ዘ ኢንተርንሺፕ” መጥቀስ ይቻላል፡፡ ፊልሙ በፈጠራ ሃሳቦች የተሞላ እና ከስራ ገበታቸው ላይ የተቀነሱ ወጣት ስራተኞች ላይ ያተኮረ ነው፡፡ ወጣቶቹ በዘመናዊ የቴክኖሎጂ ለውጥ ምክንያት ከስራ ተቀነሱ፡፡ በኋላ በጎግል ካምፓኒ ስራ ለማግኘት ጥረት ሲያደርጉ፣ ፈጠራቸውና ሃሳባቸው ተቀባይነት ሲያገኝ ያሳያል፡፡  ከዚህ ፊልም በኋላ በርካታ ወጣቶችም በተስፋ አዳዲስ ሃሳቦችን መመኮራቸው፣ አእምሯዊ ፈጠራቸውን በመጠቀማቸው ስኬታማ መሆናቸውን ያሳያል፡፡ በአጠቃላይ ኪነ ጥበብ እውኑ ዓለም ወደፊት ምን ሊመስል እንደሚችል በመተንበይ ትልቅ አበርክቶ አለው፡፡

በጊዜው አማረ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review