AMN-የካቲት 30/2017 ዓ.ም
በታሪካዊው እና በኢትዮጵያዊያን የጀግንነት ታሪክ ትልቅ ቦታ ባለው አድዋ ድል የተሠየመው የአድዋ ድል ማይክሮ ፋይናንስ አክሲዮን ማህበር ዛሬ የኢፌዴሪ ጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ በተገኙበት በመከላከያ መኮንኖች ክበብ በይፋ ተመሥርቷል።
ምስረታውን ያበሰሩት ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ በተቋሙ ከ2002 ዓ.ም ጀምሮ አክሲዮን ማህበር እንዲቋቋም ጥረት ሲደረግ መቆየቱን እና አሁን ላይ በቀጥታ ወደ ሥራ በመግባት አክሲዮን ማህበሩን መመሥረት ሥለመቻሉ ገልፀዋል።
የመከላከያ ፋውንዴሽን ሪፎርሙን ተከትሎ እንደአዲስ ከተደራጀ ወዲህ በበርካታ ዘርፎች ለሠራዊቱ የማህበራዊ ዋስትና ሆኖ እየሠራ ስለመሆኑም ጠቁመዋል።

የአድዋ ድል አክሲዮን ማህበር የተቋሙን የፋይናንስ ሴክተር ለማሣደግ የሚያግዝ ከመሆኑም በላይ የሠራዊቱን ፋይናንሻል ተጠቃሚነት የሚያሳድግ በመሆኑ በሁሉም ቦታ ተደራሽ ለማድረግ ቅርንጫፎች ማብዛት ፈጣን አገልግሎት ሠጪ ለመሆን መሥራት ያስፈልጋልም ብለዋል።
አክሲዮን ማህበሩ በጠንካራ ዲስፕሊን የሚመራ መሆን እንዳለበት ያመላከቱት ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ
ሁሉም የመከላከያ ሠራዊት አባላትን ጨምሮ የልማት ድርጅቶች የባንኩ ተጠቃሚ መሆን እንደሚገባቸውም አስገንዝበዋል።
የአክሲዮን ማህበሩ አደራጅ ኮማቴ ሰብሳቢ ብርጋዲየር ጄኔራል ደረጀ መገርሳ የአክሲዮን ማህበሩ ፅህፈት ቤት ጨምሮ ስድስቱ አደራጅ የልማት ድርጅቶች የብሄራዊ ባንክን የአሠራር መሥፈርት በተከተለ አግባብ ከፍተኛ አክሲዮን ከመግዛት ጀምሮ አደራጅ ኮማቴዎችን በመሰየም ያለመታከት ቀን ከሌሊት በመሥራት ለምሥረታው ዕውን መሆን አሥተዋፅኦ ያበረከቱ በመሆናቸው ምስጋና ማቅረባቸውን ከኢፌዴሪ መከላከያ ሰራዊት ማኀበራዊ ትስስር ገፅ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።