AMN-መጋቢት 1/2017 ዓ.ም
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ደንብ ማስከበር ባለስልጣን ከአካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን ጋር በመተባበር ፍሳሽ ቆሻሻ ወደ ወንዝ የለቀቁ ድርጅቶችና ግለሰቦች በደንብ ቁጥር 180/2017 መሰረት የገንዘብ ቅጣቶች በመቅጣት አስተዳደራዊ ርምጃ መውሰዱን አስታውቋል፡፡
ባለስልጣኑ በዛሬው እለት በቂርቆስ ክፍለ ከተማ 3 ድርጅቶች እያንዳንዳቸው 300,000/ሶስት መቶ ሺህ/ ብር በድምሩ 900,000/ዘጠኝ መቶ ሺህ ብር እና አንድ ግለሰብ 100,000/አንድ መቶ ሺህ/ ብር በድምሩ 1 ሚሊዮን ብር ቀጥቷል፡፡
በተመሳሳይ በአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ 700 ሺህ ብር ፤በነፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ 300 ሺህ ብር ፤ በጉለሌ ክፍለ ከተማ 300 ሺህ ብር በድምሩ በዛሬው እለት 2300,000/ሁለት ሚሊየን ሶስት መቶ ሺህ ብር/ በመቅጣት አስተዳደራዊ ርምጃ መውሰዱን ከባለስልጣን መስርያ ቤቱ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።

ባለስልጣኑ ተቋማት እና ግለሰቦች ማንኛውም አይነት ፍሳሽ ቆሻሻ ወደ ወንዝ በመልቀቅም ሆነ ደረቅ ቆሻሻ ወንዝ ውስጥ በመጣል ደንብ በመተላለፍ ከሚወሰደው የቅጣት ርምጃ እራሳቸውን እንዲጠብቁ አሳስቧል።
ድርጊቱን በሚፈፅሙ ግለሰቦችና ተቋማት ላይ በደንብ ቁጥር 180/2017 መሠረት የሚወሰደው እርምጃ አጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታውቋል።
ህብረተሰቡም ደንቡን ተላልፎ የሚገኝ አካል ሲመለከት በነፃ የስልክ መስመር 9995 ጥቆማ እንዲሰጥ ጥሪ አስተላልፏል።