AMN – የካቲት 16/2017 ዓ.ም
ብልፅግና ፓርቲ ህብረተሰቡን በማሳተፍ እና በማስተባበር በርካታ የህዝብ ጥያቄዎችን እየመለሰ መሆኑን የኦሮሚያ ክልል ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ አወሉ አብዲ ተናገሩ።
በቦንጋ ከተማ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች የተሳተፉበት አገር አቀፍ የህዝብ ኮንፍረንስ እየተካሄደ ነው።
በመድረኩ የኦሮሚያ ክልል ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ አወሉ አብዲ፣ የጋምቤላ ክልል ምክትል ፕሬዝዳንት ጋትሉዋክ ሮን (ዶ/ር)፣ በብልጽግና ፓርቲ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ሀላፊ አቶ ፍቅሬ አማን እና ሌሎች የመንግስት አመራሮች ተገኝተዋል።
የኦሮሚያ ክልል ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ አወሉ አብዲ፣ ብልፅግና ፓርቲ ህብረተሰቡን በማሳተፍና በማስተባበር በርካታ ጥያቄዎች መልሷል ብለዋል።
ፓርቲው በመጀመሪያው መደበኛ ጉባዔው ያስቀመጣቸውን አቅጣጫዎች እና ውሳኔዎችን መሰረት በማድረግ በርካታ ስኬቶች መመዝገባቸውን ገልጸዋል።
የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል በአዲስ መልክ እንዲደራጅ መደረጉም አንዱ ማሳያ ነው ብለዋል።

በብልፅግና ፓርቲ ሁለተኛ መደበኛ ጉባዔው ላይ የተቀመጡ አቅጣጫዎች እና ውሳኔዎች ላይም የጋራ አረዳድ በመያዝ እና በመስማማት ቀጣይ ሀገራዊ ግቦችን ለማሳካት በጋራ መትጋት እንደሚገባ ጠቁመዋል።
መድረኩ ባለፉት ዓመታት የተመዘገቡ ውጤታማ ስራዎችን የበለጠ ለማጠናከር መዘጋጀቱን ያነሱት ደግሞ በብልጽግና ፓርቲ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ሀላፊ አቶ ፍቅሬ አማን ናቸው።
ውይይቱ ከሁሉም የህብረተሰብ ክፍሎች ጋር በመምከር እና በመግባባት በየአካባቢው ያሉ ፀጋዎችን በማልማት ለቀጣይ ጉዟችን መንገድ የሚጠርግ እንደሆነ መግለፃቸውን ኢዜአ ዘግቧል።