ፓርቲው በመጀመሪያ ጉባኤው ያስቀመጣቸው አቅጣጫዎችና ውሳኔዎች ስኬታማ ናቸው-ርዕሰ መስተዳድር ኦርዲን በድሪ

You are currently viewing ፓርቲው በመጀመሪያ ጉባኤው ያስቀመጣቸው አቅጣጫዎችና ውሳኔዎች ስኬታማ ናቸው-ርዕሰ መስተዳድር ኦርዲን በድሪ

AMN-የካቲት 15/2017 ዓ.ም

የብልጽግና ፓርቲ በመጀመሪያ ጉባኤው ያስቀመጣቸው አቅጣጫዎችና ውሳኔዎች ስኬታማ መሆናቸውን የፓርቲው ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባልና የሀረሪ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ኦርዲን በድሪ ገለጹ።

“ከቃል እስከ ባህል” በሚል መሪ ሃሳብ በሁለተኛው የብልጽግና ፓርቲ መደበኛ ጉባኤ ውሳኔዎችና አቅጣጫዎች ላይ ያተኮረ ህዝባዊ ውይይት በወላይታ ሶዶ ከተማ እየተካሄደ ነው።

በመድረኩ አቶ ኦርዲን በድሪ፥ፓርቲው በመጀመሪያው ጉባኤ ያስቀመጣቸው አቅጣጫዎችና ውሳኔዎች ስኬታማ ናቸው ብለዋል።

ለዚህም የአመራሩና የህዝቡ ቅንጅትና በባለቤትነት መምራት ለስኬቱ ጉልህ ድርሻ ማበርከቱን ገልጸው፥ፓርቲው ያስቀመጣቸው ውሳኔዎች በተጨባጭ መሬት ላይ በመውረዳቸው ተስፋ ሰጪ ልማቶች መታየታቸውን ተናግረዋል።

የተጀመሩ ውጤቶችን በማጠናከር ሁለንተናዊ ብልጽግናን ለማረጋገጥ ፓርቲው በትኩረት እየሰራ ነው ብለዋል፡፡

ለዚህም ፓርቲው በቅርቡ ባካሄደው 2ኛ ጉባኤ የተለያዩ እቅጣጫዎችንና ውሳኔዎችን ማሳለፉን ጠቅሰው፥ ወጥ በሆነ መልኩ ተፈጻሚ እንዲሆኑ ህዝባዊ ውይይቱ ጠቃሚ መሆኑን ገልጸዋል።

የፓርቲው ሥራ አሥፈጻሚ ኮሚቴ አባልና የአማራ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አብዱ ሁሴን (ዶ/ር) በበኩላቸው፣ “ከፈተና ወደ ልዕልና” በሚል መሪ ሀሳብ በተካሄደው በመጀመሪያው ጉባኤ በተቀመጡ አቅጣጫዎች ፖለቲካዊ፣ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ድሎች መመዝገባቸውን አንስተዋል።

የህዳሴ ግድብን ጨምሮ ብሔራዊ ጥቅምን የሚያስከብሩ ሀገራዊ ፋይዳ ያላቸውና የዜጎችን የልማት ጥያቄ የመለሱ ሥራዎች መከናወናቸውን ጠቁመዋል።

ይሁን እንጂ ነጻነትን በአግባቡ ከማስተዳደር አንጻር በታዩ ክፍተቶች አገልግሎት አሰጣጥና መሰል ጉድለቶች መስተዋላቸውን ጠቅሰዋል።

በጉድለት የተለዩ ጉዳዮችን በብቃት በመፍታት ሀገርን ወደ ልዕልና ለማሻገር እንዲቻል ”ከቃል እስከ ባህል” በሚል መሪ ሃሳብ በ2ኛው የፓርቲ ጉባኤ አቅጣጫ መቀመጡን ተናግረዋል።

በዚህም በሁሉም ዘርፎች የላቀ ስኬት ለማስመዝገብ የነቃ ተሳትፎ አስፈላጊ መሆኑን አክለዋል።

የመድረኩ ተሳታፊዎች ለውይይት መነሻ በቀረቡ ነጥቦች ላይ ሀሳብና አስተያየት እየሰጡ መሆኑን ከክልሉ ኮሙኒኬሽን የተገኘ መረጃ ያመላክታል።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review