AMN – መጋቢት 5/2017 ዓ.ም
ባሳለፍነው ሳምንት የዩክሬኑ ፕሬዚዳንት ቮሎድሚር ዜለንስኪ ከአሜሪካ ጋር ባደረጉት ውይይት የተኩስ አቁም ለማድረግ መስማማታቸውን ተከትሎ የሩሲያው ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲንም የ30 ቀን የተኩስ አቁም ዕቅድ ላይ እንደሚስማሙ አስታውቀዋል፡፡
ይሁንና የተኩስ አቁም ዕቅዱ ወይይት የሚሹ ጥያቄዎች አሉት ብለዋል፡፡
በዚሁ ጉዳይ ላይ የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ልዩ መልዕክተኛ ስቲቭ ዊትኦፍ ከፕሬዚዳንት ፑቲን ጋር ለመነጋገር ሀሙስ እለት ወደ ሞስኮ አቅንተው ነበር ተብሏል፡፡
የታቀደው ውይይት ስለመካሄዱ የተባለ ነገር ባይኖርም ሀሙስ ምሽቱን ሩሲያ እና ዩክሬን የድሮን ጥቃት ሲሰነዛዘሩ አንግተዋል፡፡
በሀገራቱ መካከል በተካሄደው አዲስ የድሮን ጥቃት በሰሜናዊ ዩክሬን 7 ሰዎች ከባድ ጉዳት ሲደርስባቸው በደቡባዊ ሩሲያ የነዳጅ ማሳለጫ ላይ ጉዳት መድረሱ ተሰምቷል፡፡
ፑቲን ትላንት በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ “ተኩስ አቁም ስምምነት ትክክል እና የምንደግፈው ነው፣ ነገር ግን ልንነጋገርባቸው የሚገቡ ጥያቄዎች አሉ” ብለዋል፡፡
ስምምነቱ ወደ ጠንካራ ሠላም የሚመራ እና የቀውሱን መሠረታዊ ችግርም ያስወግዳል ያሉት ፕሬዚዳንት ፑቲን “ከአሜሪካ አጋሮቻችን ጋር መስማማት ይገባል፣ ምናልባትም ከፕሬዚዳንት ትራምፕ ጋር የስልክ ውይይት ሳላደርግ አልቀርም” ማለታቸውን ቢቢሲ ዘግቧል፡፡
የ30 ቀን ተኩስአቁም ዕቅድ በተለይም ለዩክሬናዊያን ትልቅ ጥቅም እንዳለው አንስተው እኛም ይህን የምንደግፈው ነው ብለዋል፡፡
እንደ ፕሬዚዳንት ፑቲን፣ የ30 ቀን የተኩስ አቁም ስምምነት በምን አግባብ እንደሚመራ፣ ጦርነቱ እንዲቆም ትዕዝዘ የሚያስተላልፈው አካል የትኛው ነው፣ አጠቃላይ ሁኔታዎች በምን አግባብ ቁጥጥር ይደረግባቸዋል የሚሉ እና ሌሎችም በርካታ ጉዳዮች ውይይት የሚሹ ናቸው፡፡
የፑቲንን መግለጫ ተከትሎ የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ትራምፕ ከሩሲያ አቻቸው ጋር ለመነጋገር ዝግጁ መሆናቸውን የገለጹ ሲሆን፣ ሩሲያ ትክክለኛ ድምዳሜ ላይ እንደምትደርስ ተስፋ አደርጋለሁ ብለዋል፡፡
በማሬ ቃጦ