ፕሬዝዳንት ታየ አጽቀሥላሴ የጥራት መንደርን ጎበኙ

AMN-ታህሳስ 1/2017 ዓ.ም

ፕሬዝዳንት ታየ አጽቀሥላሴ በቅርቡ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የተመረቀውን የተለያዩ የጥራት መሰረተ ልማት ተቋማት በአንድ ላይ የሚገኙበትን የጥራት መንደር ጎብኝተዋል።

የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር የጥራት መሰረተ ልማት ማረጋገጫ ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ እንዳለው መኮንን ጨምሮ የንግድ ሥርዓትና ላይሳንሲንግ ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር አብዱልሃኪም ሙሉ እና የጥራት መሠረተ ልማት ተቋማት አመራሮች ለፕሬዝዳንቱ አቀባባል በማድረግ ስለ ጥራት መንደሩ ገለጻ አድርገውላቸዋል፡፡

በንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር የጥራት መሰረተ ልማት ማረጋገጫ ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ እንዳለው መኮንን፣ የጥራት መንደሩ በኢፌዲሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ሃሳብ አመንጪነት እንደተጀመረ በመግለጽ ለመንደሩ ግንባታ 8 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር ወጪ የተደረገበትና ጥራትን የሚያረጋግጡ ዘመናዊ የላብራቶሪና የቢሮ ግንባታ የያዘ መሆኑን ለፕሬዝዳንቱ ገለጻ አድርገዋል፡፡

የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር የንግድ ሥርዓትና ላይሳንሲንግ ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር አብዱልሃኪም ሙሉ በበኩላቸው፣ የጥራት መንደሩ የገቢና ወጪ ምርቶችን ጥራት በማረጋገጥ ለሀገር ኢኮኖሚ ዕድገት ያለው ፋይዳ የጎላ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ፕሬዝዳንቱ በጥራት መንደሩ የሚገኙ ተቋማት በጤና ዘርፍ፣ በኮንስትራክሽን፣ በግብርና ውጤቶች፣ በምግብና መጠጥ ዘርፎች እና በኢንዱስትሪ ግብዓቶችና በተለያዮ ዘርፎች ገቢና ወጪ ምርቶችን እና አገልግሎቶችን ጥራት የሚያረጋግጡ የላብራቶሪ መሳሪያዎችን ተዘዋውረው ጎብኝተዋል፡፡

በጉብኝቱም ባዩት ነገር መደሰታቸውን መናገራቸውን የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር መረጃ ያመላክታል።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review