AMN – ታኀሣሥ 18/2017 ዓ.ም
የፅንፈኛውን ቡድን የጥፋት ተልዕኮ ተከትለን ባደረስነው ሰብዓዊና ቁሳዊ ጉዳት ተፀፅተን ህዝቡን ለመካስ ተመልሰናል ሲሉ የክልሉ መንግስትን የሠላም ጥሪ ተቀብለው የተመለሱ የፅንፈኛው ቡድን አባላት የነበሩ ተናገሩ።
በሰሜን ጎንደር ዞን ሲንቀሳቀሱ የቆዩ የፅንፈኛ ቡድን አባላት የነበሩ ከ900 በላይ ታጣቂዎች ወደ ህብረተሰቡ ተቀላቅለው ሰላማዊ ህይወት መምራት የሚያስችላቸውን የተሃድሶ ስልጠና በዳባት ከተማ መከታተል ጀምረዋል።
የፅንፈኛው ቡድን በክልሉ መንገድ በመዝጋት፣የመማር ማስተማር ስራውን በማስተጓጎልና ሌሎች የልማት ተግባራትን በማደናቀፍ በህዝብ ላይ በደል ሲፈፅም ቆይቷል።
ቡድኑ በሰላማዊ መንገድ፣ችግሩን በውይይትና በመነጋገር መፍታት እንዲችል የክልሉ መንግስት ተደጋጋሚ የሰላም አማራጭ ጥሪ ማቅረቡ ይታወሳል።
የሰላም ዋጋ የገባቸውና በዕኩይ ድርጊታቸው የተፀፀቱ የፅንፈኛ ቡድን አባላት ህዝባቸውን በልማት ለመካስ የመንግስትን የሰላም ጥሪ ተቀብለው ወደ ሰላማዊ ኑሮ እየገቡ ይገኛል።
የሰላም ጥሪውን ተቀብለው በመመለስ በተለያዩ አካባቢዎች የተሃድሶ ስልጠና መውሰድ ከጀመሩት መካከል የዳባት ከተማ የተሀድሶ ማሰልጠኛ ማዕከል ሰልጣኞች ይገኙበታል።
በሰሜን ጎንደር ዞን ዳባት ከተማ በሚገኘው የስልጠና ማዕከል የገባው የፅንፈኛ ቡድኑ አባል የነበረው ሽፈራው ዘመዴ፤ ”የተከተልነው የጥፋት መንገድ በህዝባችን ላይ ሞት መፈናቀልና የንብረት ውድመት አስከትሏል” ሲል ተናግሯል።
ሰላማዊ ትግልን አማራጭ በማድረግ የመንግስትን የሠላም ጥሪ ተቀብሎ መመለሱን ጠቅሶ፤ በቀጣይም ሳያውቅ የበደለውን ህዝብ በልማት ለመካስ መዘጋጀቱን ነው ያረጋገጠው።
ግጭቱ ሰብዓዊና ቁሳዊ ጉዳት ከማድረስ በዘለለ በትምህርት ቤቶች መዘጋት ሳቢያ ልጆች ከትምህርት ገበታ መለየታቸው ቁጭት እንዳሳደረበት የገለጸው ደግሞ ሌላው የተሃድሶ ሰልጣኝ ወጣት ቴዎድሮስ ወለላው ነው።
ፅንፈኛው ቡድን የተከተለው የትግል አካሄድ ትውልድ ገዳይና ልማት አውዳሚ መሆኑን በመገንዘብ የጥፋት ተልዕኮው አስፈጻሚ ላለመሆን ወስኖ መምጣቱን አስታውቋል።
ሀብታም ብቅአየሁ በበኩሏ፤ የቡድኑ ተልዕኮና ዓላማ ከህዝብ ጥቅምና ፍላጎት ያፈነገጠ መሆኑን በመረዳት ተከትለውት ከነበረው አጥፊ ድርጊቷ መመለሷን ተናግራለች።
“ለህዝብ እታገላለሁ” በሚል የተሳሳተ መንገድ በህዝብ ላይ እየደረሰ ያለው በደልና ሰቆቃ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ እንዲያበቃ በመፈለግ የሰላሙን ጥሪ ተቀብላ መግባቷን አረጋግጣለች።
ሰላማዊ የትግል አማራጭ እያለ በአፈሙዝ ሃይል ብቻ የህዝብን ፍላጎትና ጥያቄ ማሳካት እንደማይቻል ጠቁማ፥ ሰላማዊ ትግልን አማራጭ በማድረግ የሰላም ጥሪውን መቀበሏን ገልፃለች።
የተሃድሶ ሰልጣኞቹ ጫካ ያሉ ወንድሞቻችን የህዝባቸው ሰቆቃና እንግልት እንዲቆም የሰላም ጥሪውን ተቀብለው እንዲገቡም ጥሪ አቅርበዋል።
የዳባት ከተማ የተሀድሶ ማሰልጠኛ ማዕከል አስተባባሪ አቶ ፋሲል ድልነሳ እንዳሉት፥ የመንግስትን የሰላም ጥሪ ተቀብለው በሰላማዊ መንገድ የገቡት ከ900 በላይ የፅንፈኛ ቡድኑ አባላት ናቸው።
የቡድን አባላት በአጥፊ ድርጊታቸው ተፀፅተው ወደ ሰላማዊ አማራጭ መምታጣቸው ቡድኑ ትክክለኛ የትግል መንገድ እየተከተለ እንዳልሆነ ማሳያ ነውም ብለዋል።
ሌሎችም ሲገባቸው “የእነዚህን አርዓያነት ይከተላሉ” ብለን እናስባለን ያሉት አስተባባሪው፤በስልጠና ቆይታቸውም በአገራዊና በክልሉ ወቅታዊ ሁኔታ እንዲሁም በሰላም እሴት ግንባታ ላይ ያተኮረ ስልጠና ይሰጣቸዋል።
ሰልጣኞቹ ወደ ህብረተሰቡ ከተቀላቀሉ በኋላም ሰላማዊ ህይወት የሚመሩበትና የበደሉትን ህዝብ መካስ የሚችሉበት ሁኔታ እንደሚመቻች ማስታወቃቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
የክልሉ መንግስት ፅንፈኛው ቡድን ችግሩን በመነጋገር መፍታት እንዲችል በተደጋጋሚ ጥሪ ማቅረቡ ይታወሳል።