AMN – ታኀሣሥ 19/2017 ዓ.ም
በመዲናዋ ትልልቅ ከተሞች የሚያሟሉትን ልማት የሚያሟላ ስራ እየተሰራ መሆኑን መመልከታቸውን ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ በከተማዋ የተገነቡ የልማት ሥራዎችን በጎበኙበት ወቅት ገልጸዋል፡፡
በወንዝ ዳርቻ ልማት እየተሰራ ያለው ስራ ትልቅ መሆኑን የገለጹት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በተለይም እንጦጦ ላይ የኮንሶ ወጣቶች በአጭር ጊዜ የሰሩት ስራ አስደናቂ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በአራዳ ክፍለከተማ የተገነቡ ትልልቅ ዓለም አቀፍ የማራቶን ውድድሮችን ማስተናገድ የሚችሉ ፕሮጀክቶች ፣ የብስከሌት መንገዶች እና የቱሪዝም ልማቱን ለማስፋፋት የሚያስችል ስራ እየተሰራ መሆኑን መመልከታቸውን አንስተዋል፡፡
በመዲናዋ በስኬት እየተከናወነ የሚገኘው የኮሪደር ልማት ስራም ፈጠራና ፍጥነትን አስተሳስሮ እየተከናወነ መሆኑን ተመልክተናል ነው ያሉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ፡፡
ለካሳንችስ ኮሪደር ልማት ተነሺዎች የተገነባው የገላን ጉራ መንደር የአካባቢው ነዋሪዎች ከዚህ ቀደም ይኖሩበት የነበረውን ያልተመቻቸ የኑሮ ዘይቤ የቀየረ እና በዚህም ነዋሪዎች መደሰታቸውን አይተናል ብለዋል፡፡
በተለይም በመንደሩ የተማሪዎችና የአረጋውያን ምገባ እንዲሁም ትምህርት ቤት እና የህጻናት መጫወቻ ስፍራዎች መገንባታቸው የሚያስመሰግን መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ብልጽግና ሰው ተኮር ነው ስንል ተንከባካቢ ያጡ አረጋውያንን የመደገፍ እንዲሁም የነገ ሀገር ተረካቢ ህጻናትን ማስተማር ነው ሲሉ ገልጸዋል፡፡
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በመዲናዋ ላከናወናቸው ሰው ተኮርና ዘርፈ ብዙ የልማት ስራዎች ምስጋና አቅርበዋል፡፡