AMN – ታኅሣሥ 22/2017 ዓ.ም
በሀገሪቱ የኤሌክትሪክ አገልግሎትን የተሻለ ተደራሽ ለማድረግና ፍትሀዊነትን ለማረጋገጥ ከተለመደው ይልቅ ዘመናዊ አሰራርን መከተል እንደሚገባ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አስገንዝቧል፡፡
ምክር ቤቱ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል እና የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ተቋማት የስራ አፈጻጸምን በሚመለከት ከተቋማቱ የስራ ኃላፊዎች ጋር ውይይት አድርጓል፡፡
የምክር ቤቱ አባላት በህዝብ ውክልና ስራቸው ከመረጣቸው ህዝብ የመብራት አገልግሎትን በሚመለከት ያሰባሰቧቸውን ጥያቄዎች በማንሳት የተቋማቱ የስራ ኃላፊዎች ማብራሪያ ሰጥተውበታል፡፡
በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግስት ተጠሪ ሚኒስቴር ዲኤታ ወ/ሮ መሰረት ሃይሌ፤ በተለያዩ የሀገሪቱ አከባቢዎች የኤሌክትሪክ አገልግሎትን የተሻለ ተደራሽ ለማድረግና ፍትሀዊነትን ለማረጋገጥ ከተለመደው በመውጣት ዘመናዊ አሰራርን መከተል እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡
በተቋማቱ የተጀመሩ ስራዎች ተስፋ ሰጭ መሆናቸውን የጠቀሱት ወ/ሮ መሰረት፤ ያሉትን ጉድለቶች በየዘርፉ ማስተካከል እንደሚገባና የኤሌክትርክ መሠረተ ለማቶች ላይ ተገቢው ጥበቃ ሊደርግላቸው እንደሚገባ አሳስበዋል::
በቀጣይም እንደ ሀገር የተጀመረውን የሪፎርም ስራ መነሻ በማድረግ በገጠርም ሆነ በከተማ ፍትሀዊ ተደራሽነትን እና ጥራትን ለማረጋገጥ የተጀመረውን ጥረት በእቅድ በመምራት ማጠናከር እንደሚገባም አስገንዝበዋል፡፡
ቋሚ ኮሚቴው ባዘጋጀው የህዝብ ውክልና ማብራሪያ ላይ የኤሌክትሪክ አገልግሎትን ለማስፋፋት ህብረተሰቡ እና የከተማ አስተዳደሮች በትብብር መስራት እንደሚገባቸው የመንግስት የልማት ድርጅቶች ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ የተከበሩ ፕሮፌሰር መሐመድ አብዱ አመላክተዋል።
የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ እንዳሉት የኤሌክትሪክ አገልግሎትን ለማስፋፋት ህብረተሰቡ እና የከተማ አስተዳደሮች በትብብር መስራት እንደሚገባቸው አስገንዝበዋል፡፡
በጥራት ጉድለትና የሃይል መቆራረጥ፣ የመሰረተ ልማቶች መጎዳትና ሌሎችም ጥያቄዎች ተነስተው ከተቋማቱ በመጡ አመራሮች ምላሽ ተሰጥቶባቸዋል።
የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ዋና ስራ አስፈፃሚ ኢንጂነር ሽፈራሁ ተሊላ ለቀረቡት ጥያቄዎች ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡
በኪራይ ስብሳቢነት ችግሮች ዙርያ ለተነሱ ጥያቄዎች ሪፎርም እየተደረገባቸው መሆኑን ጠቅሰው፣ በቀጣይም ከደንበኞች አገልግሎት ጋር ተያይዞ ያሉ ችግሮች እንደማይቀጥሉ መጠቆማቸውን ከምክር ቤቱ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።