AMN – ታኀሣሥ 24/2017 ዓ.ም
ባለፈው ክረምት ወቅት በኢትዮጵያ ጎርፍ መከላከል ፕሮጀክት የተሰራው የአስቸኳይ ጊዜ የቅድመ-ጎርፍ መከላከል ስራ ጥሩ ውጤት ማስገኘቱን በውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የውሃ ሀብት አስተዳደር ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ አብርሃ አዱኛ (ዶ/ር) ገለጹ።
ሚኒስትር ዴኤታው የጎርፍ መከላከል ስራ በተለይ ከ2014 ዓመተ ምህረት ጀምሮ በመንግስት በጀት ሲሰራ እንደነበር እና በበጀት እጥረት ምክንያት ጎርፉ እርሻና መሠረተልማት ላይ የሚያስከትለውን ጉዳት ሙሉ በሙሉ መቆጣጠር አለመቻሉን ገልጸዋል፡፡
ከዓለም ባንክ በተገኘ የገንዘብ ድጋፍ ባለፈው ክረምት ወቅት በአዋሽ ወንዝ ላይ የተሰራው የአስቸኳይ ጊዜ የቅድመ-ጎርፍ መከላከል ስራ ይከሰት የነበረውን ጉዳት በእጅጉ መቀነሱን አብራርተዋል።
በላይኛው፣ በመካከለኛው እና በታችኛው አዋሽ ላይ 151 ኪሎ ሜትር ዳይክ የተሰራ መሆኑን ገልጸው፤ በቀጣይ ጊዜያትም በተቀሩት ቦታዎች ላይ የቅድመ-ጎርፍ መከላከል ስራ እንደሚሰራ ጠቁመዋል፡፡
የጎርፍ መከላከል ሥራው የልማት ስራዎችን ታሳቢ ባደረገ መልኩ በጊዜ ለመስራት ከክልል ከዞንና ከወረዳ አመራሮች እንዲሁም ከማህበረሰቡ ጋር በተዋረድ ውይይቶች እየተደረጉ መሆኑን አንስተዋል።
በኦሞ ወንዝና በሪፍት ቫሊ ሀይቆችም የዲዛይን ጥናቶች እየተደረጉ መሆኑን ገልጸዋል።
የአዋሽ ቤዚን አስተዳደር ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ አደን አብዶ በበኩላቸው የአዋሽ ወንዝ የማህበረሰቡ ተስፋ መሆኑን አንስተው፤ የተሰራው የቅድመ-ጎርፍ መከላከል ስራ ማህበረሰቡን ከምንጊዜውም በላይ ያስደሰተ መሆኑን ገልጸዋል።
በቀጣይም ልዩ ትኩረት የሚፈልጉ ቦታዎችን ከክልሉ አመራሮች ጋር ለይተን ዝግጁ አድርገናል ብለዋል።
ለቀጣይ ስራዎችም ክረምት ከመግባቱ በፊት ባለድርሻ አካላትን አቀናጅቶ ወደ ስራ እንደሚገባ አቅጣጫ መቀመጡን ከሚኒስቴሩ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።