ጃፓን በኢኮኖሚው መስክ ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን ግንኙነት ይበልጥ ለማጠናከር ትሰራለች፡- አምባሳደርን ሺባታ ሂሮኖሪ

You are currently viewing ጃፓን በኢኮኖሚው መስክ ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን ግንኙነት ይበልጥ ለማጠናከር ትሰራለች፡- አምባሳደርን ሺባታ ሂሮኖሪ

AMN – ታኅሣሥ 24/2017 ዓ.ም

ኢትዮጵያና ጃፓን በኢኮኖሚው መስክ ያላቸውን ግንኙነት ይበልጥ ለማጠናከር እንደሚሠሩ የጃፓን አምባሳደርን ሺባታ ሂሮኖሪ አመለከቱ ፡፡

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቴዎስ (ዶ/ር ) በኢትዮጵያ የጃፓን አምባሳደር ሺባታ ሂሮኖሪን በጽህፈት ቤታቸው ተቀብለው አነጋግረዋል።

በውይይቱ ላይ ሚኒስትሩ የኢትዮ-ጃፓን ግንኙነት አንድ ክፍለ ዘመን ያስቆጠረ እና ታሪካዊ መሆኑን በመግለጽ ኢትዮጵያ ከጃፓን ጋር ያላትን ግንኙነት የበለጠ ለማጠናከር ቁርጠኛ መሆኗን አንስተዋል።

ዶ/ር ጌዲዮን ጃፓን በኢኮኖሚ ልማት እና በቴክኒክ ትብብር ትርጉም ያለው ድጋፍ ስታደርግ መቆየቷን በውይይቱ ላይ ገልጸዋል።

ሚኒስትሩ በተለይ በአሁኑ ወቅት የቀድሞ ታጣቂዎችን ትጥቅ በማስፈታት ወደ የተሀድሶ ስልጠና በመስጠት ወደ ማኀበረሰቡ እንዲቀላቀሉ (DDR) የሚደረገውን እንቅስቃሴ ፣ ለመልሶ ግንባታ እና መልሶ ማቋቋሚያ ሥራዎች የምታደርገውን ድጋፍ አጠናክራ እንድትቀጥል ጠይቀዋል።

በአሁኑ ወቅት ተግባራዊ እየተደረገ ያለው ሁሉን አቀፍ የኢኮኖሚ ማሻሻያ ምቹ የኢንቨስትመንት ዕድል የፈጠረ በመሆኑ የጃፓን ኩባንያዎች እንዲሳተፉ ሚኒስትሩ ጥሪ አቅርበዋል።

ዶ/ር ጌዲዮን የቶኪዮ ዓለም አቀፍ የአፍሪካ ኮንፈረንስ (TICAD) ለአፍሪካ ጃፓን ግንኙነት ወሳኝ መድረክ በመሆኑ ኢትዮጵያ ድጋፏን እንደምትቀጥል ገልጸዋል።

አምባሳደር ሺባታ ሂሮኖሪ በበኩላቸው የኢትዮጵያ እና ጃፓን ግንኙነት በተለይ በኢኮኖሚ መስክ ይበልጥ በሚጠናከርበት መንገድ ላይ እንደሚሠሩ ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ በቀጣናው ሰላም እና ፀጥታ ለማስፈን የምትሠራውን ሥራ አገራቸው እንደምትደግፍ መናገራቸውን ከሚኒስቴሩ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review