ሞዴል የአርብቶ አደሮች መንደር መገንባቱ የአርብቶ አደሩን ኑሮ ከከተሜነት ጋር በማስታረቅ ረገድ የእሳቤ ለውጥን ያመጣል፡- አቶ ሙስጠፌ መሐመድ

You are currently viewing ሞዴል የአርብቶ አደሮች መንደር መገንባቱ የአርብቶ አደሩን ኑሮ ከከተሜነት ጋር በማስታረቅ ረገድ የእሳቤ ለውጥን ያመጣል፡- አቶ ሙስጠፌ መሐመድ

AMN – ታኅሣሥ 26/2017 ዓ.ም

የሶማሌ ክልል ፕሬዚዳንት አቶ ሙስጠፌ መሐመድ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ተመርቆ አገልግሎት መስጠት የጀመረውን የጅግጅጋውን ሞዴል የአርብቶ አደሮች መንደር አስመልክተው አስተያየት ሰጥተዋል።

አቶ ሙስጠፌ በሰጡት አስተያየትም ሞዴል የአርብቶ አደሮች መንደር መገንባቱ የአርብቶ አደሩን ኑሮ ከከተሜነት ጋር በማስታረቅ ረገድ የእሳቤ ለውጥን ያመጣል ብለዋል።

የአርብቶ አደሩ ሕይወት እየተለወጠ እና የከተሜነት ተፅእኖው እየመጣ መሆኑን ያመለከቱት የሶማሌ ክልል ፕሬዝደንት አቶ ሙስጠፌ መሐመድ በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት አርብቶ አደሩ ወደ ከተሞችና አካባቢው እየፈለሰ መሆኑንም ጠቁመዋል።

ከአየር ንብረት ለውጡ ጋር እያጋጠማቸው ያለውን የውኃ እና ግጦሽ እጥረት ለማቃለል የከተሜነት ፍላጎትን እና የአየር ንብረት ለውጡን ተፅእኖ ታሳቢ በማድረግ ችግሩን የሚፈታ ሞዴል የአርብቶ አደር መንደር ተገንብቷል ብለዋል።

መንደሩ አርብቶ አደሩን የውኃ፣ መብራት እና መንገድን የመሰሉ የመሠረተ ልማቶች ተጠቃሚ የሚያደርጋቸው ሲሆን በመንደሩ ከአርብቶ አደሮቹ በተጨማሪ ለእንስሳቱም ቤት መገንባቱን አመልክተዋል።

በክልሉ እየተመዘገበ ካለው ፈጣን ዕድገት አርብቶ አደሩም ተጠቃሚ በመሆን የትምህርት፣ የመብራትና መሰል ልማቶች ተጠቃሚ ለማድረግ የዘመናዊ መንደሮቹ መስፋፋት ጠቀሜታው የጎላ ነው።

ይህ ሞዴል ዘመናዊ መንደር የአርሶ አደሩንና የአርብቶ አደሩን የገበያ ፍላጎት በማቀራረብ ትስስር ይፈጥራልም ብለዋል አቶ መስጠፌ።

በሽመልስ ታደሰ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review