AMN – ታኅሣሥ 26/2017 ዓ.ም
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የጥቁር አንበሳ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ያስገነባውን የድንገተኛ ህክምና ማዕከል አስመርቋል።
ማዕከሉ የጤና ሚኒስትር ዶክተር መቅደስ ዳባ፣ የትምህርት ሚኒስትርና የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ቻንስለር ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ፣ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተጠባባቂ ፕሬዚዳንት ሳሙኤል ክፍሌ (ዶ/ር)ን ጨምሮ ሌሎች እንግዶች በተገኙበት ነው የተመረቀው።
የጤና ሚኒስትር ዶክተር መቅደስ ዳባ እንዳሉት፥ ማዕከሉ የሆስፒታሉን የድንገተኛ ህክምና አገልግሎት ተደራሽነትን ለማስፋት ጉልህ ሚና ይኖረዋል።
ለድንገተኛና ህክምና ፈጣን ምላሽ ለመስጠት የሚያስችሉ መሰረተ ልማቶችና ባለሙያዎች ማፍራት ላይ ትኩረት መሰጠቱን ገልጸዋል።
የትምህርት ሚኒስትርና የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ቻንስለር ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ በበኩላቸው፥ በጤናና በትምህርት ዘርፍ የተጀመሩ ሪፎርሞች ዝቅተኛ ገቢ ያላቸውን የህብረተሰብ ክፍሎች ተጠቃሚ የሚያደርጉ ናቸው ብለዋል።
የመንግሥት የህክምና ተቋማትን አቅም ለማጠናከርና የተሻለ አገልግሎት መስጠት የሚያስችሉ አቅሞችን ለመፍጠር ከጤና ሚኒስቴር ጋር በትብብር እየተሠራ መሆኑን ገልጸዋል።
የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተጠባባቂ ፕሬዚዳንት ሳሙኤል ክፍሌ (ዶ/ር)፥ ዩኒቨርሲቲው የጥቁር አንበሳ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታልን የልህቀት ማዕከል ለማድረግ እየሰራ መሆኑን ማንሳታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
የጥቁር አንበሳ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ባለፉት ስድስት ወራት ግማሽ ሚሊዮን ለሚጠጉ ዜጎች የህክምና አገልግሎቶችን መስጠቱ ተገልጿል።