
AMN-ታህሣሥ 26/2017 ዓ.ም
የምዕራብ ዕዝ ኮር አዛዥ ብርጋዲየር ጄኔራል አዘዘው መኮንን ኮሩ ከሚገኝበት ምስራቅ ጎጃም ዞን በእነብሴ፣ በባሶሊበን፣በሸበል በረንታና በደጀን ወረዳ ዙሪያ ያሉ አስራ አራት ቀበሌዎችን ያካለለ አሰሳ በማድረግ በደቡብ ጎንደር አዋሳኝና አባይ በርሀን ይዞ እስከ ዛንባራ የሚባሉ ባታዎች ድረስ በመሰማራትና ጠላት እስከሚሸሸግባቸው በርሀዎች ዘልቆ በመግባት በወሰደው ተከታታይ የማጥቃት እርምጃ አመርቂ ውጤት ማስመዝገብ መቻሉን ገልፀዋል።

ሠራዊቱ በፅንፈኛው ላይ ከባድ ምት በማሳረፍ ሰላሳ አባላቱ ሲገደሉ ዘጠኝ በማቁሰልና ዘጠኝ በመማረክ የተለያዩ ዓይነት መሣሪያዎችንና ተተኳሾችን በቁጥጥር ስር ማዋል መቻሉንም ተናግረዋል።
ከዚህ በተጨማሪ ፅንፈኛው ቡድን ሲጠቀምበት የነበረው ወታደራዊ አልባሳት፣ የስልጠና ማንዋል፣ ስድስት ሞተር ሳይክል፣17800 ብር ከአምስት የወደመ ሞተር ሳይክል ጋር መያዙንም አብራርተዋል።
ኮሩ በአጭር ጊዜ እንዲያጠናቅቅ በተሰጠው ግዳጅ መሠረት የፅንፈኛውን ግብአተ መሬት በማፋጠን የበላይነቱን እያረጋገጠ ባለበት ተግባሩ ተከታታይ ለማድረግ በትኩረት እንደሚሰራ ጄኔራል መኮንኑ ገልፀዋል።
የክፍለ ጦር ምክትል አዛዥ ለውጊያ ድጋፍ አገልግሎት ሌተናል ኮሎኔል ታደሰ ረጋሳ በበኩላቸው የፅንፈኛው ከፍተኛ አመራር ፈንታ አቡዋን ከነጄሌው በመግደል አምስት አባላቱን መማረክ እንደተቻለ መግለጻቸውን ከመከላከያ ሰራዊት ማህበራዊ የትስስር ገጽ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።