ተረጂነት ቀጣይነት እንዳይኖረው ተግተን እንሰራለን -ከንቲባ አዳነች አቤቤ

AMN – ታኅሣሥ 27/2017 ዓ.ም

የ2ኛ ምዕራፍ የከተማ የምግብ ዋስትና ተጠቃሚዎች ሽግግር ሥነ-ስርዓት “ከተረጂነት ወደ ምርታማነት” በሚል መሪ ሀሳብ ተካሂዷል።

በመርኀግብሩ ላይ የተገኙት የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ፣ ተረጂነት ቀጣይነት እንዳይኖረው በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

“የምንሰራው የምግብ እና ኢኮኖሚያዊ ሉዓላዊነታችንን ለማረጋገጥ ነው” ያሉት ከንቲባ አዳነች “ይህንን ለማድረግ ብርቱዎች ነን ለዚህም ማሳያው የዕለቱ ተመራቂዎች ናቸው” ብለዋል።

አዲስ አበባ ሸማች ብቻ ሳትሆን አምራች መሆን መቻሏን በመግለጽ ተመራቂዎች በተሻለ ትጋት የተሻለ ደረጃ ሊደርሱ እንደሚገባ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡

154 ሺ ዜጎች ቀጣዩን ዙር የሚጀምሩ መሆኑን የገለጹት ከንቲባዋ ይህም መንግስት የዜጎችን ኑሮ እና አኗኗር ለመቀየር ያለውን ፍላጎት ያሳያልም ብለዋል።

በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የስራ እና ክህሎት ቢሮ ኃላፊ አቶ ጥራቱ በየነ በበኩላቸው ፣ በአለም ባንክ እና በፌዴራል መንግስት ድጋፍ በመዲናዋ የከተማ ልማት ሴፍትኔት ተጠቃሚዎች ከ216 ሺ በላይ መሆናቸውን ገልጸዋል።

እነዚህ ዜጎች በከተማዋ ውበት እና ጽዳት ውስጥ የላቀ አበርክቶ ሲያደርጉ የቆዩ መሆናቸውንም ገልጸዋል።

በዛሬው እለትም በሁለተኛው ምዕራፍ የከተማ የምግብ ዋስትና እና ስራ ፕሮጀክት ከ31 ሺ በላይ ተጠቃሚዎች ለተከታታይ ሶስት አመታት በፕሮጀክቱ ሲሰጥ የነበረውን ድጋፍ በማጠናቀቅ ለምርቃት በቅተዋል ብለዋል።

ለተመራቂዎቹ በመረጡት የስራ መስክ የስራ እድል መመቻቸቱም ተመላክቷል፡፡

በሃብታሙ ሙለታ

All reactions:

4747

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review