
AMN – ታኅሣሥ 27/2017 ዓ.ም
በአዲስ አበባ ከተማ በማደያዎች የተስተዋሉ የተሽከርርካሪ ሰልፎች በነዳጅ አቅርቦት ውስንነት የተፈጠሩ ሳይሆን በማደያዎች የስርጭት ክፍተት የተከሰቱ መሆናቸውን የአዲስ አበባ ንግድ ቢሮ አስታወቀ።

የቢሮው የገበያ መረጃ ጥናት እና የፕሮሞሽን ዳይሬክተር የሆኑት አቶ ሙሰማ ጀማል ለኤ ኤም ኤን እንደገለጹት፣ መዲናዋ አስተማማኝ የነዳጅ አቅርቦት አላት።
በነዳጅ ማደያዎች ነዳጅ እያለ “ነዳጅ የለም” የሚሉ እና መስተጓጎልን የሚፈጥሩ ማደያዎችን በተጨባጭ በመለየት እርምጃ እንደሚወሰድም ገልጸዋል።
ኅብረተሰቡን በሐሰተኛ መረጃዎች የሚያደናግሩ በከተማዋ የነዳጅ አቅርቦት ክፍተት እንዳለ አስመስለው የሐሰት መረጃን የሚነዙ እንዳሉ ይገመታል ብለዋል ዳይሬክተሩ።
ኅብረተሰቡ ትክክለኛ መረጃን ከቢሮው ሕጋዊ ገፅ እና ከታማኝ መረጃዎች በመውሰድ ከመደናገር ራሱን እንዲጠብቅ መክረዋል።
አዲስ አበባ የዓለም የስበት ማዕከል፣ የአፍሪካ መናገሻ እና የኢትዮጵያዊያን የአብሮነት መድመቂያ እንደመሆኗ በርካታ እንቅስቃሴዎች እንደሚደረጉባት አውስተዋል።
የአዲስ አበባ ንግድ ቢሮ ከፌዴራል መንግሥት ጋር በቅንጅት በቂ የነዳጅ አቅርቦትን እንደሚያሠራጭም ነው የገለጹት።
በቀጣይም በማደያዎች ላይ ያለውን አግባብነት የሌለው የስርጭት አካሄድ እና ነዳጅ እያለ የለም የሚሉ ላይ እርምጃ እንደሚወሰድ አቶ ሙሰማ አሳስበዋል።
በተመስገን ይመር