አየር ሃይል ሃገራዊ ግዳጅ እና ተልዕኮውን በብቃት እየተወጣ ይገኛል-ሌተናል ጄኔራል ይልማ መርዳሳ

You are currently viewing አየር ሃይል ሃገራዊ ግዳጅ እና ተልዕኮውን በብቃት እየተወጣ ይገኛል-ሌተናል ጄኔራል ይልማ መርዳሳ

AMN – ታኅሣሥ 28/2017 ዓ.ም

አየር ኃይል እያከናወናቸው የሚገኙ ዘርፈ ብዙ የስራ እና የግዳጅ አፈፃፀም እንቅስቃሴዎች ውጤታማ መሆናቸውን የኢፌዴሪ አየር ሃይል ዋና አዛዡ ሌተናል ጄኔራል ይልማ መርዳሳ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ አየር ኃይል በየዘመናቱ ሁሉ የተሰጡትን ሃገራዊ ግዳጅ እና ተልዕኮዎችን በአስተማማኝ ብቃት እየተወጣ ዛሬ ላይ የደረሰ በድል እና በመስዋዕትነት የደመቀ አኩሪ ታሪክ ያለው አንጋፋና ስመ ገናና የአቭዬሽን ተቋሙ ነው ያሉት ሌተናል ጄኔራል ይልማ መርዳሳ አሁንም ዘመኑን በዋጀ መልኩ ተደራጅቶ የኢትዮጵያን የአየር ክልል በንቃት እየጠበቀ እንደሚገኝ ገልፀዋል፡፡

ተቋሙ ዘመናዊ የስልጠና ሂደትን በመከተል ብቃት ያላቸው ተተኪ ባለሙያዎችን ለማፍራት ትኩረቱን የአየር ኃይል አካዳሚ ላይ በማድረግ የዘመኑን የአቭዬሽን ቴክኖሎጂ መጠቀም የሚችሉ በርካታ ባለሙያዎችን እያፈራ የሚገኝ መሆኑንም ገልፀዋል። አመራሩም የተጀመሩ ሁሉን አቀፍ ስራዎች አጠናክሮ እንዲቀጥል አሳስበዋል ፡፡

“ለታላቅ ሃገር ታላቅ አየር ኃይል” በሚል መርህ የኢትዮጵያን ታላቅነት የሚመጥን ተቋም ለመገንባት እንዲቻል በሰው ኃይል አቅም ግንባታ፣በውጊያ መሰረተ ልማት ግንባታ፣አዳዲስ ትጥቆችን በመታጠቅ እና በማሻሻል እንዲሁም ምቹ እና ፅዱ የስራ አካባቢን በመፍጠር ረገድ ባከናወናቸው የለውጥ ስራዎች አመርቂ ውጤቶችን ማስመዝገብ መቻሉንም ዋና አዛዡ ገልፀዋል፡፡

የኢትዮጵያ አየር ኃይል በ2022 ከአፍሪካ ቀዳሚ ተመራጭ የአቭዬሽን ተቋም ለማድረግ የተያዝነው ራዕይ በትክክለኛው መስመር እየተጓዘ መሆኑንም መናገራቸውን ከኢፌዴሪ መከላከያ ሰራዊት ማኅበራዊ ትስስር ገጽ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

የኢትዮጵያ አየር ኃይል በአሁኑ ወቅትም ሀገራችንን ከውጭም ሆነ ከውስጥ የጥፋት ቡዱኖች ለመከላከል በሚያስችል ቁመና ላይ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review