
AMN – ታኀሣሥ 28/2017 ዓ.ም
የቦሌ ክፍለ ከተማ አስተዳደር የገናን በዓል ምክንያት በማድረግ በክፍለ ከተማው ለሚኖሩ አቅመ ደካማ ወገኖች ማዕድ አጋርቷል፡፡
የክፍለ ከተማ አስተዳደሩ አስተባባሪዎች በተገኙበት ከሁሉም ወረዳዎች ለተውጣጡ ከአንድ ሺህ በላይ አቅመ ደካማ ወገኖች የማዕድ ማጋራት ተደርጓል፡፡

የቦሌ ክፍለ ከተማ አስተዳደር ዋና ሥራ አስፈጻሚ ወ/ሮ ዓለምጸሐይ ሺፈራው በመርሐ ግብሩ ላይ ባስተላለፉት መልዕክት፣ ኢትዮጵያዊ የመረዳዳትና የመተጋገዝ ባሕላችንን በማጎልበት በበዓላት ወቅት ለአቅመ ደካማ ወገኖቻችን ማዕድ ስናጋራ ከፍ ያለ ደስታ ይሰማናል” ብለዋል።

በሀገር አቀፍና በአዲስ አበባ ደረጃ በማዕድ ማጋራት በርካታ ወገኖች ተጠቃሚ መሆናቸውን ያወሱት ዋና ሥራ አስፈጻሚዋ፣ በዘንድሮው የገና በዓል የማዕድ ማጋራት ድጋፍ የተደረገላቸው ወገኖች መልካም በዓል እንዲያሳልፉ መልካም ምኞታቸውን ገልጸዋል፡፡
ለመርሐ ግብሩ መሳካት በማስተባበርና ድጋፍ በማድረግ ለተባበሩ አካላትም ምስጋና አቅርበዋል።
የቦሌ ክፍለ ከተማ አስተዳደር ኅብረተሰብ ተሳትፎና በጎ ፍቃድ ማስተባበሪያ ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ጌታቸው ካሣዬ በበኩላቸው፣ በዓሉን አስመልክቶ በአጠቃላይ ከ37 ሺ በላይ ለሆኑ ወገኖች በአጋር አካላት ድጋፍ ማዕድ መጋራቱን መናገራቸውን ከክፍለከተማው ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

All reactions:
4848