ለነገዋ የሴቶች ተሃድሶ እና ክህሎት ማበልጸጊያ ማዕከል ከሚቀጥለው በጀት ዓመት ጀምሮ እስከ 10 ሺህ ሰልጣኞችን ማሰልጠን ይጀምራል- ከንቲባ አዳነች አቤቤ

You are currently viewing ለነገዋ የሴቶች ተሃድሶ እና ክህሎት ማበልጸጊያ ማዕከል ከሚቀጥለው በጀት ዓመት ጀምሮ እስከ 10 ሺህ ሰልጣኞችን ማሰልጠን ይጀምራል- ከንቲባ አዳነች አቤቤ

AMN – ጥር 1/2017 ዓ.ም

ለነገዋ የሴቶች ተሃድሶ እና ክህሎት ማበልጸጊያ ማዕከል ከሚቀጥለው በጀት ዓመት ጀምሮ በሙሉ አቅሙ ወደ ስራ በመግባት በዓመት እስከ 10 ሺህ የሚደርሱ ሰልጣኞችን ማሰልጠን እንደሚጀምር የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ ገለጹ።

ማዕከሉ ለተለያዩ ማህበራዊ ችግሮች የተጋለጡ እና በአስቸጋሪ ሁኔታ ኑሯቸውን ሲመሩ የነበሩ 400 የሁለተኛ ዙር ሰልጣኞችን ተቀብሏል።

ወደ ማዕከሉ የሚገቡ ሴቶች በራሳቸው ጥፋት ሳይሆን በተሳሳተ የማህበረሰቡ ግንዛቤ ለችግር ተጋልጠው የነበሩ መሆናቸውን የተናገሩት ከንቲባዋ፣ ለተለያዩ ማህበራዊ ጫናዎች ተጋልጠው ውስጣቸው ያለውን እምቅ አቅም እንዳያወጡ ሆነው ቆይተዋል ብለዋል።

ለነገዋ የሴቶች ተሃድሶና የክህሎት ማበልጸጊያ ማዕከል ለነዚህ ሴቶች መጠጊያ እና ተስፋ ሆኖ ሰብአዊ ክብራቸው ተጠብቆ ስልጠና በማግኘት ውስጣቸው ያለውን እምቅ አቅምና ችሎታ አውጥተው ወደ ስራ እንዲሰማሩ እና ራሳቸውን ችለው ህይወታቸው እንዲቀየር ማድረጉን አንስተዋል።

በማዕከሉ ስልጠና የሚያገኙ ሴቶች የማይገባቸውን የሚያገኙ ሳይሆኑ እንደዜጋ በፍትሃዊነት ከሀገሪቱ ሀብት ተጠቃሚ የሚሆኑበት እንደሆነም ጠቁመዋል፡፡

ማንኛውም ልማት የሚሰራው ለሰው ነው ያሉት ከንቲባ አዳነች፣ ሁለንተናዊ ጥረት የሚደረገውም ከድህነት ለመውጣት እንደሆነና ለነገዋን የመሳሰሉ ተቋማት ደግሞ የሰውን ህይወት በመቀየር ውስጥ አስተዋጿቸው ከፍተኛ መሆኑን አመላክተዋል።

የሁለተኛ ዙር ሰልጣኞች በተመቻቸላቸው እድል ጊዜያቸውን በአግባቡ በመጠቀም ውጤታማ ሊሆኑ እንደሚገባም አስገንዝበዋል።

በማዕከሉ ሰልጣኞች ውጤታማ እንዲሆኑ እና ራሳቸውን እንዲችሉ ድጋፍ ላደረጉ አካላትም ምስጋና አቅርበዋል።

በመጀሪያው ዙር በ17 አይነት የስልጠና መስኮች ሰልጥነው ወደ ስራ የተሰማሩ ከ300 በላይ ሰልጣኞች ስኬታማ የሆኑ ሲሆን የህይወት ተሞክሯቸውንም ለአዳዲሶቹ ሰልጣኞች አካፍለዋል።

በሰብስቤ ባዩ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review