AMN – ጥር 1/2017 ዓ.ም
የአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን (አሚኮ) የሚዲያ ኢንዱስትሪው የልህቀት ደረጃ ላይ ለመድረስ እያደረገ ያለው ጥረት የሚበረታታ መሆኑን በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የርዕሰ መስተዳድሩ የሕዝብ ግንኙነት አማካሪ እና የአሚኮ የሥራ አመራር ቦርድ ሰብሳቢ አቶ ይርጋ ሲሳይ ገለጹ።
አሚኮ ያስገነባው ተንቀሳቃሽ የቀጥታ ስርጭት ማስተላለፊያ ስቱዲዮ ዛሬ አስመርቋል።
በምረቃ ሥነ-ሥርዓቱ አቶ ይርጋ ሲሳይ እንደገለጹት፤ አሚኮ የክልሉ ብሎም የሀገሪቱን ሕዝቦች የኑሮ ደረጃ እንዲሻሻል በተሞክሮ ልውውጥ እና አዳዲስ አሠራሮችን በማስተዋወቅ የድርሻውን እየተወጣ ይገኛል።
በዚህም በክልሉ የሚካሄደው የኢንዱስትሪ፣ የግብርና እና ሌሎች የልማት ሥራዎች እንዲፋጠኑ እና የሕዝቡ የኑሮ ደረጃ እንዲሻሻል ያበረከተውን አስተዋጽኦ ጠቅሰዋል።
የተሳሳቱ ትርክቶች ታርመው ኅብረ ብሔራዊነት እንዲሰርጽ ሁሉንም ያሳተፈ ውይይት እና ክርክር በማካሄድ በሕዝቦች መካከል መግባባት እንዲፈጠር የጎላ ሚና መወጣቱን ተናግረዋል።
በቀጣይም የጀመራቸውን ተግባራት ይበልጥ በማጠናከር እና የዘመኑ የሚዲያ ኢንዱስትሪ የደረሰበትን መረጃን በጥራት እና በፍጥነት የማሠራጨት ተግባር ለማከናወን ያስገነባው ተንቀሳቃሽ የቀጥታ ስርጭት ማስተላለፊያ ቴክኖሎጂ ፋይዳው የጎላ ነው ብለዋል።
የክልሉ መንግስትም የአሚኮ የሪፎርም ተግባር ተጠናክሮ እንዲቀጥል አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ አረጋግጠዋል።
በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የከተሞች ዘርፍ አስተባባሪና የክልሉ የከተማና መሰረተ ልማት ቢሮ ሃላፊ፣ የአሚኮ የሥራ አመራር ቦርድ ምክትል ሰብሳቢ አህመዲን መሃመድ(ዶ/ር) በበኩላቸው፤ አሚኮ የዘመኑን የሚዲያ ውድድር መቀላቀሉን የሚያረጋግጥ ተግባራት እያከናወነ መሆኑን ተናግረዋል።
ይህም “ወደ ቴክኖሎጂ ልህቀት” በሚል አሁን ላይ በአቅም ግንባታ፣ በቴክኖሎጂ ማስገባትና ተደራሽነት፣ በመረጃ ቅልጥፍናና ጥራት ላይ እያደረገ ያለውን ጥረት በመጥቀስ አመላክተዋል።
የሚዲያ ኢንዱስትሪው ፈጣንና ተለዋዋጭ በሆነበት በዚህ ዘመን ኮርፖሬሽኑ በየጊዜው አሠራሩንና አደረጃጀቱን በማዘመን ለክልሉ ብሎም ለሀገር ግንባታና ለሕዝብ ተጠቃሚነት መሥራቱን አጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ገልጸዋል።
በተለይም አሚኮ ሰላምን ማፅናት ላይ ትኩረት በማድረግ ታጣቂዎች ወደ ሰላም አማራጭ እንዲመጡ የበለጠ መሥራት እንዳለበት አመልክተዋል።
አሚኮ ከ30 ዓመት በፊት በበኩር ጋዜጣ ሥራ ጀምሮ አሁን ላይ በሰባት ራዲዮና ሁለት የቴሌቪዥን ጣቢያዎች መረጃዎችን በተለያዩ ቋንቋዎች ለማሠራጨት የበቃ ድርጅት መሆኑን የገለጹት ደግሞ የአሚኮ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ሙሉቀን ሰጥዬ ናቸው።
በዚህም የክልሉን ብሎም የሀገሪቱ የልማት ሥራዎች እንዲፋጠኑ በመረጃ ልውውጥ ያበረከተው አስተዋጽኦ በሁሉም ሕዝብ ዘንድ ተቀባይነት እንዲያገኝ አስችሎታል ብለዋል።
ኮርፖሬሽኑ ዛሬ ያስመረቀው ተንቀሳቃሽ የቀጥታ ስርጭት ማስተላለፊያ ስቱዲዮ በፖለቲካ፣ በኢኮኖሚና በማህበራዊ መስኮች መረጃን በጥራትና በፍጥነት ተደራሽ ለማድረግ እንደሚያስችለው ተናግረዋል።
አሚኮ ያስገነባው የቀጥታ ስርጭት ማስተላለፊያ ስቱዲዮ በሀገራችን ሶስተኛው ሚዲያ ያደርገዋል ያሉት ደግሞ የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ባለስልጣን ምክትል ዳይሬክተር አቶ ግዛው ተስፋዬ ናቸው።
ይህም መረጃዎችን ለዓለም ተደራሽ ማድረግ የሚያስችል አቅም የፈጠረ መሆኑን ጠቁመው፤ ባለስልጣኑ ለሚዲያው እድገት አጋዥ ተግባራትን በማከናወን የበኩሉን እየተወጣ እንደሚገኝ መግለጻቸውን የዘገበው ኢዜአ ነው።
በምረቃ ሥነ-ሥርዓቱ የፌዴራል እና የክልሉ ከፍተኛ አመራር አባላት እና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።