
AMN – ጥር 3/2017 ዓ.ም
የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሌጅ 874 የ29ኛ ዙር መደበኛ የፖሊስ ሰልጣኞችን ከንቲባ አዳነች አቤቤ በተገኙበት አስመርቋል።
ተመራቂዎቹ 225 ሰዓት የክፍል ውስጥ እና 480 ሰዓት የመስክ በአጠቃላይ የ764 ሰዓት ፖሊሳዊ ስልጠናዎችን የወሰዱ መሆናቸው ተገልጿል።
በምረቃ መርሃ ግብሩ ላይ የተገኙት የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ፣ የአዲስ አበባ ፖሊስ አገልግሎት ተደራሽነት ከግዜ ወደ ግዜ እያደገ እና እየሰፋ መምጣቱን ተናግረዋል።

ከለውጡ በኋላ በጸጥታ ተቋማት የተሰራውን ሪፎርም ተከትሎ የአዲስ አበባ ፖሊስ በከተማዋ ያለውን የህዝብ ቁጥር ታሳቢ ባደረገ ልክ አገልግሎቱን እንዲያሳድግ በሎጀስቲክስ የማጠናከር ፣ በሰው ሀይል የማሳደግ እና በዘመናዊ ቴክኖሎጂ የማስታጠቅ ተግባራት ሲከናወኑ መቆየታቸውን ከንቲባ አዳነች ተናግረዋል።
የፖሊስ አገልግሎት ተደራሽነትን ለማስፋት የፖሊስ ጣቢያዎችን ቁጥር በእጥፍ የማሳደግ ፣ የፖሊስ መምሪያዎችንም በአዲስ የመገንባት እና ለስራ ምቹ የማድረግ ተግባራት መከናወናቸውን የተናገሩት ከንቲባዋ የዛሬዎቹ ተመራቂዎችም ፖሊሳዊ አገልግሎትን በቅርበት ለህዝብ ከማድረስ አንጻር ከፍተኛ አስተዋጽኦ ይኖራቸዋል ብለዋል።
ተመራቂ የፖሊስ አባላቱ ህብረተሰቡን በቅንነት እና በታማኝነት ያለ ልዩነት እንዲያገለግሉ ብሎም የተወሳሰበውን የወንጀል ተግባር ፖሊሳዊ ጥበብን እና ቴክኖሎጂን ብሎም ልዩ ልዩ ስልቶችን በመጠቀም መከላከል እንደሚገባቸውም አሳስበዋል።

በሰብስቤ ባዩ