በመዲናዋ የከተራ እና ጥምቀት በዓል ስኬታማ ሆኖ እንዲጠናቀቅ የሰላም መዋቅሩ ዝግጅት አጠናቋል- የሰላም እና ጸጥታ አስተዳደር ቢሮ

AMN – ጥር 3/2017 ዓ.ም

የከተራ እና ጥምቀት በዓል ስኬታማ ሆኖ እንዲጠናቀቅ የሰላም መዋቅሩ ዝግጅት ማጠናቀቁን የአዲስ አበባ ከተማ ሰላም እና ጸጥታ አስተዳደር ቢሮ አስታወቀ።

የአዲስ አበባ ከተማ ሰላም እና ጸጥታ አስተዳደር ቢሮ የጥምቀት በዓል አከባበር የጸጥታ ሁኔታ ቅድመ ዝግጅትን በማስመልከት ከአዲስ አበባ ሰላም እና ጸጥታ አስተዳደር ቢሮ እና ከደንብ ማስከበር ባለስልጣን አመራሮች ጋር እየተወያየ ነው።

በመድረኩ ላይ መልዕክት ያስተላለፉት የአዲስ አበባ ከተማ ሰላም አና ጸጥታ አስተዳደር ቢሮ ኃላፊ ወይዘሮ ሊዲያ ግርማ፣ የከተራ እና ጥምቀት በዓል ፍጹም ሰላማዊና ስኬታማ ሆኖ እንዲጠናቀቅ የሰላም መዋቅሩ ዝግጅት ማጠናቀቁን ገልጸዋል።

የከተማዋን የልማት እንቅስቃሴ ያለምንም የጸጥታ ችግር እንዲካሄዱ ውጤታማ ስራዎች መከናወናቸውን የገለጹት ኃላፊዋ ልማቶቹን ለማስቀጠል የሚያስችል የሰላም እና ጸጥታ ስራ አጠናክሮ ማስቀጠል ያስፈልጋል ብለዋል።

ህዝብን የሰላሙ ባለቤት ማድረግ እና በስፋት ማሳተፍ በሰላም እና ጸጥታው ዘርፍ ለተገኘው ውጤት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማድረጉንም ገልጸዋል።

መጪው የከተራ እና ጥምቀት በዓል ሀይማኖታዊ ዕሴቱን በጠበቀ መልኩ እንዲከበር በርካታ ስራዎች እየተከናወነ መሆኑን የጠቆሙት ኃላፊዋ ለዚህም ይረዳ ዘንድ በዓሉን በባለቤትነት ከምታከብረው ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ጋር በጋራ በመሆን እየተሰራ ነው ብለዋል።

በበዓሉ ወቅት በቴክኖሎጂ የተደገፈ የሰላም እና ጸጥታ ማስከበር ስራ ይከናወናልም ብለዋል።

በሃብታሙ ሙለታ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review