AMN – ጥር 7/2017 ዓ.ም
በተለያዩ አካባቢዎች የመንግሥትና የህዝብን የሰላም ጥሪ የተቀበሉ የቀድሞ ታጣቂዎች መደበኛ ህይወታቸውን እንዲመሩ መልሶ የማቋቋም ተግባራት ተጠናክረው መቀጠላቸውን የብሔራዊ ተሀድሶ ኮሚሽን ኮሚሽነር ተመስገን ጥላሁን ገለጹ።
ኮሚሽነሩ ይህን ያሉት በአማራ ክልል የቀድሞ ታጣቂዎች የተሀድሶ ስልጠናና መልሶ ማቋቋም ሂደት በማዕከላዊ ጎንደር ዞን ጭልጋ ወረዳ የሳራባ ማዕከል በተጀመረበት ወቅት ነው።
የሰላም አማራጭ ችግሮችን በሰከነ መንፈስ ለመፍታት ወሳኝ መንገድ መሆኑን ገልጸው፥ ታጣቂዎች የመንግሥትንና የህዝብን የሰላም ጥሪ እየተቀበሉ መሆናቸው ለሀገር ትልቅ ተስፋ ነው ብለዋል።
ወደ ተሃድሶ ማዕከል የገቡ የቀድሞ ታጣቂዎችም ህዝቡን ለመካስ ዝግጁ መሆናቸውን አሳይተዋል ያሉት ኮሚሽነሩ፥ ይህም በጫካ ለሚገኙ የታጠቁ ቡድኖች ትምህርት የሚሰጥ መሆኑን አንስተዋል።
ኮሚሽኑ የቀድሞ ታጣቂዎች መደበኛ ህይወታቸውን እንዲመሩ ለማስቻል በትግራይ፣ በአፋር፣ በኦሮሚያና በአማራ ክልሎች የተለያዩ ተግባራትን እያከናወነ እንደሚገኝም ገልጸዋል።
የመልሶ ማቋቋምና የድጋፍ ሥራዎችም ተጠናክረው መቀጠላቸውን ነው የጠቆሙት።

የብሔራዊ ተሀድሶ ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር ብርጋዴር ጄኔራል ደርቤ መኩሪያው፤ የቀድሞ ታጣቂዎች አለመግባባትን በንግግር ለመፍታት መወሰናቸው የሰላምን ዋጋ መገንዘባቸውን ያረጋገጠ መሆኑን ገልጸዋል።
ሀገር የመገንባት አካል መሆን ዕድለኝነትና ታሪካዊ ኃላፊነት ነው ያሉት ምክትል ኮሚሽነሩ፥ የቀድሞ ታጣቂዎችም ያገኙትን መልካም እድል በመጠቀም የሰላምና የልማት ሃይል እንዲሆኑ አስንዝበዋል።
የሀገር ሽማግሌዎች ተወካይ አቶ እያዩ ጀምበር፥ አለመግባባት ቢኖር እንኳ በመነጋገር መፍትሔ ማምጣት እንደሚቻል ነው ያነሱት።

በጠብመንጃ ወይም በኃይል የሚፈታ ችግር እንደሌለ በማንሳት፥ በጫካ የሚንቀሳቀሱ የታጠቁ ቡድኖች ለሰላም ቅድሚያ እንዲሰጡ ጠይቀዋል።
ሰላም ካለ ልማት ይኖራል ያሉት አቶ እያዩ፥ ሁሉም አካል ለክልሉ ህዝብ ሰላም ቅድሚያ መስጠት እንዳለበት ተናግረዋል።
ወደ ተሃድሶ የገቡ የቀድሞ ታጣቂዎች ተወካይ ሰለሞን አስማረ፥ ግጭትና የኃይል አካሄድ ማንንም እንደማይጠቅም በመገንዘብ የሰላም ጥሪውን መቀበላቸውን ገልጿል።
የተሃድሶ ስልጠናውን አጠናቀው ሲወጡም ከዚህ ቀደም የበደሉትን ማህበረሰብ ለመካስ መዘጋጀታቸውን ማንሳቱን ኢዜአ ዘግቧል።