AMN – ጥር 7/2017 ዓ.ም
በጉለሌ ክፍለ ከተማ በሁለተኛ ዙር የሚለማው ከሽሮ ሜዳ – እንጦጦ ቦታኒክ ጋርደን 6 ኪሎ ሜትር የኮሪደር ልማት ፕሮጀክት በተቀመጠለት ጥራት እና የጊዜ ገደብ ለመጨረስ ርብርብ እየተደረገ መሆኑን የጉለሌ ክፍለ ከተማ አስተዳደር አስታወቀ፡፡
የጉለሌ ክፍለ ከተማ ምክር ቤት የኮሪደር ልማት ፕሮጀክቱ በፍጥነት እና በጥራት እንዲጠናቀቅ እየተጉ ለሚገኙ ሰራተኞች የእራት ግብዣ አድርጓል።
በመርሃ ግብሩ ላይ የጉለሌ ክፍለ ከተማ ምክር ቤት አፈ – ጉባዔ አቶ መኩሪያ ጉሩሙ እየተከናወነ ያለውን ሁለተኛው ዙር የኮሪደር ልማት ከዳር ለማድረስ እየሰሩ ለሚገኙ አመራሮች፤ ባለሙያዎች ኮንትራክተሮችና ተቋማት ድጋፍ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸዋል።
የጉለሌ ክፍለ ከተማ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ወልዴ ወገሴ በበኩላቸው የእራት ግብዣ መርሃ ግብሩ ዋና ዓላማ የኮሪደር ልማት ስራውን በፍጥነት እና በጥራት እየሰሩ የሚገኙ እጆችን ለማበረታታት’ አለኝታነታችንን ለማሳየት እና ፕሮጀክቱ እስኪጠናቀቅ ከጎናችሁ ነን ለማለት ነው ብለዋል፡፡
በጉለሌ ክፍለ ከተማ ምክር ቤት አዘጋጅነት በተዘጋጀው በዚህ የእራት ግብዣ መርሃ ግብር ላይ በስራው ላይ የሚሳተፋ ባለሙያዎችና የሚያስተባብሩ አመራሮች መሳተፋቸውን ከክፍለ ከተማው ምክር ቤት የተገኘው መረጃ ያመለክታል።