AMN – ጥር 7/2017 ዓ.ም
የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ስራ በማህበረሰቡ ዘንድ መለመድ ያለበትና የዘወትር ተግባር ሆኖ ሊቀጥል እንደሚገባ የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ-ጉባዔ አቶ አገኘሁ ተሻገር ገለፁ።
በፍትህ ሚኒስቴርና በተጠሪ ተቋማት አማካኝነት በጋምቤላ ከተማ በበጎ ፈቃድ አገልግሎት የተሰሩ አምስት የአቅመ ደካሞች ቤቶች ተጠናቀው የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ-ጉባዔ አቶ አገኘሁ ተሻገር በተገኙበት ዛሬ ለተጠቃሚዎች ተላልፈዋል።
አፈ ጉባዔው በዚሁ ወቅት እንዳሉት መንግስት የህብረተሰቡን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ባለፉት የለውጥ አመታት ሰው ተኮር በሆኑ የልማት ስራዎች ላይ ትኩረት አድርጎ ሲሰራ ቆይቷል።
በተለይም በክረምቱ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ጧሪና ደጋፊ የሌላቸውን አቅመ ደካማ ወገኖች ኑሮ ለማሻሻል እየተከናወኑ ያሉ ስራዎች ውጤት እየታየባቸው ይገኛል ብለዋል።
በመሆኑም በክረምቱ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት የአቅመ ደካማች ቤት ግንባታና እድሳትን ጨምሮ በአረንጓዴ አሻራ፣ በአካባቢ ፅዳት እና በሌሎችም የበጎ ፈቃድ አገልግሎት የተጀመሩ ስራዎች የዘወትር ተግባር ሊሆኑ ይገባል ነው ያሉት።
ሰው ተኮር የሆኑ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ስራዎችን በማጠናከር አቅመ ደካማ የሆኑ ዜጎችን የመደገፉ ስራ ባህል ሆኖ ሊቀጥል እንደሚገባም ተናግረዋል።
በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የጋምቤላ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ወይዘሮ ዓለሚቱ ኡሞድ በበኩላቸው የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ማህበራዊ ኃላፊነትን ለመወጣት ከሚደረጉ ተግባራት አንዱ ነው ብለዋል።
በተለይም ከሀገራዊ ለውጡ ወዲህ የተሰሩ ተግባራት በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙ የህብረተሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ እያደረጉ ይገኛሉ ነው ያሉት።
ሁሉም ዜጋ ተባብሮና ተቀናጅቶ ከሰራ የማንሻገረው ችግር አይኖርም ያሉት ርዕሰ መስተዳድሯ፤ የመደጋገፍና የመረዳዳት ባህላችንን ይበልጥ ልናጠናክር ይገባል ብለዋል።
የፍትህ ሚኒስቴርና ተጠሪ ተቋማት ወደ ክልሉ በመምጣት ላደረጉት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ስራ ወይዘሮ ዓለሚቱ ምስጋና አቅርበዋል።
የፍትህ ሚኒስትር ዴኤታ ኤርሚያስ የማነብርሃን(ዶ/ር) እንዳሉት ሚኒስቴሩና ተጠሪ ተቋማቱ በክረምት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት በደም ልገሳ፣ የአቅመ ደካማ ቤቶች እድሳት፣ የትምህርት ቁሳቁስ እና ሌሎች ድጋፎችን ሲያከናውኑ መቆየታቸውን ተናግረዋል።
በጋምቤላ ከተማ በክረምቱ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ከሶስት ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ አምስት የአቅመ ደካማ ቤቶችን ሰርተው ዛሬ ማስረከባቸውን ኢዜአ ዘግቧል።