የዓለም የእንስሳት ጤና ድርጅት የአፍሪካ አህጉራዊ ጉባኤ ከፊታችን ጥር 27 ጀምሮ በአዲስ አበባ ይካሄዳል

AMN-ጥር 7/2017 ዓ.ም

የዓለም የእንስሳት ጤና ድርጅት የአፍሪካ አህጉራዊ ጉባኤ ከፊታችን ጥር 27 እስከ 30/2017 ዓ.ም በአዲስ አበባ ይካሄዳል።

የዓለም የእንስሳት ጤና ድርጅት ጉባኤ በየዓመቱ በግንቦት ወር በፓሪስ የሚካሄድ ሲሆን በየአህጉራቱም በየሁለት ዓመቱ ይካሄዳል፡፡

በአፍሪካ ደረጃ 25ኛው ጉባኤ በቦትስዋና ርዕሰ ከተማ ጋቦሮኒ በ2023 (እ.ኤ.አ) ተካሄዷል፡፡

በኢትዮጵያ የሚካሄደው የ2025ቱ የዓለም የእንስሳት ጤና ድርጅት የአፍሪካ አህጉራዊ ጉባኤ “የእንስሳት ጤና ለምግብና ስነ ምግብ ዋስትና መረጋገጥ እና ለሕብረተሰብ ጤና” በሚል መሪ ሀሳብ እንደሚካሄድ ተገልጿል፡፡

የግብርና ሚኒስትር ዴኤታ ፍቅሩ ረጋሳ (ዶ/ር) እንደገለጹት፣ ለጉባኤው መሳካት በተደረጉ ቅድመ ዝግጅቶች መሠረት ከዓለም የእንስሳት ጤና ድርጅት ዋናው ፅ/ቤት፣ የአፍሪካ ተወካዮችና የምስራቅ አፍሪካ ተወካዮች ጋር የተለያዩ ቅድመ ዝግጅቶች ሲደረጉ ቆይቷል።

ለዚህም በግብርና ሚኒስቴር በኩል ግብረ-ሃይል ተቋቁሞ ቅድመ ዝግጅቶችን በማድረግ ላይ እንደሚገኝ ጠቁመዋል፡፡

ከ54 የአፍሪካ ሀገራት የጤና ኃላፊዎችና ቋሚ ተወካዮች፣ ከዓለም የእንስሳት ጤና ድርጅት፣ በየአህጉሩ ያሉ የእንስሳት ጤና አመራሮች፣ ዓለም አቀፍ ድርጅቶች፣ የልማት አጋሮች፣ የግሉ ዘርፍና የመንግሥት ተቋማት ተወካዮች በጉባኤው ይታደማሉም ነው የተባለው።

በጉባኤው በአፍሪካ የእንስሳት ጤና አገልግሎት፣ ድንበር ዘለል የእንስሳት በሽታዎችን መቆጣጠርና መከላከል በሚቻልበት ሁኔታ ብሎም ከበሽታ ነጻ የሆነ አህጉር ለመፍጠር የሚረዱ ውይይቶች እንደሚደረጉ ሚኒስትር ዴዔታው ተናግረዋል፡፡

በሌማት ትሩፋቱ እየተሰሩ ያሉ (ዝርያ ማሻሻል፣ መኖ፣ የእንስሳት ጤና) የሕብረተሰብ ጤና አጠባበቅ በስፋት ውይይት ይደረግበታል፤ አቅጣጫዎች ይቀመጡበታልም ሲሉ ተናግረዋል።

እንደ ሚኒስትር ዴኤታው ገለጻ በኢትዮጵያ የሚካሄደው የዓለም የእንስሳት ጤና ድርጅት የአፍሪካ ጉባኤ የእንስሳት ጤና እንዲጠበቅ ብሎም ዘርፉ እንዲነቃቃ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው ከግብርና ሚኒስቴር የተገኘ መረጃ ያመላክታል።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review