AMN – ጥር 8/2017 ዓ.ም
ባለፉት ስድስት ወራት በፈታኝ ሁኔታዎች ውስጥ አመርቂ ዲፕሎማሲያዊ ስኬቶች መመዝገባቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ገለጸ።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ነብያት ጌታቸው በወቅታዊ የዲፕሎማሲና የውጭ ግንኙነት ዙሪያ ሳምንታዊ መግለጫ ሰጥተዋል።
በመግለጫቸውም ባለፉት ስድስት ወራት በፈታኝ ሁኔታዎች ውስጥ አመርቂ ዲፕሎማሲያዊ ስኬቶች መመዝገባቸውን ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ ከጎረቤት ሀገራት ጋር ያላትን ሁለንተናዊ ትስስር የሚያጠናክሩ ተግባራት መከናወናቸውንና በቀጣናው ሰላም ማስከበር ላይ ያላት ሚና እውቅና እንዲያገኝ ማድረግ መቻሉንም ገልፀዋል።
የባህር በር ጥያቄ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅም ጉዳይ መሆኑን ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ እንዲረዳ ለማድረግ የተሰሩ ስራዎች ውጤታማ እንደነበሩም አንስተዋል።
ኢትዮጵያ ከቀጣናው ሀገራት ጋር ሁለንተናዊ ትስስሯን ለማጠናከር የሰራችበት ጊዜ እንደነበርም ጠቁመዋል፡፡
ለአብነትም ኢትዮጵያንና ደቡብ ሱዳንን የሚያገናኘውን የመንገድ ግንባታ ስምምንት ጨምሮ ኢትዮጵያ ለኬኒያ የምትልከውን የኤሌክትሪክ መጠን ለመጨመር ስምምነት ላይ መደረሱን አንስተዋል።
የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም ያስጠበቁ የተለያዩ የሁለትዮሽ ስምምነቶች መፈጸማቸውን ጠቁመው ከ128 በላይ የከፍተኛ አመራሮች ጉብኝት እና ውይይቶች መካሄዳቸውንም አንስተዋል።
በዜጋ ተኮር ዲፕሎማሲም ባለፉት ስድስት ወራት በተለያዩ ሀገራት በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ የነበሩ ከ32 ሺህ 918 በላይ ዜጎች ወደ ሀገር መመለሳቸውን ተናግረዋል።
ከአጎራባች ሀገራት ጋር ያለው የሁለትዮሽና የህዝብ ለህዝብ ግንኙነትን የሚያጠናክሩ ተግባራት መከናወናቸውንም ጠቁመዋል።
የአንካራውን ስምምነት ተከትሎ የሶማሊያ ፕሬዝዳንት ሀሰን ሼክ ሞሐሙድ በኢትዮጵያ ያደረጉት ጉብኝት የሁለቱን ሀገራት ግንኙነት ወደ ቀደመው ለመመለስ ትልቅ መደላድል የፈጠረ መሆኑንም ገልጸዋል።
ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ጋር ባደረጉት ውይይትም ሁሉቱም ሀገራት በሙሉ ውክልና ሚሲዮኖቻቸውን ዳግም ወደ ስራ ማስገባት እንደሚጀምሩ መስማማታቸውንም ጠቁመዋል።
ኢትዮጵያ እና አዘርባጃን ሶስተኛውን የፖለቲካ ምክክር ማካሄዳቸውን ነው የገለጹት፡፡
በሁለቱ ሀገራት መካከል የተካሄደው ምክክር አገራቱ በግብርና፣ ማዕድን፣ ማኑፋክቸሪንግ እና አረንጓዴ ኢኮኖሚ ዘርፎች ያላቸው ሁለንተናዊ ግንኙነት የበለጠ እንዲጠናከር የሚያግዝ መሆኑንም መጠቆማቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡