የጥምቀት በዓል ኃይማኖታዊና ትውፊታዊ እሴቱን ጠብቆ በድምቀት እንዲከበር ወጣቶች ሚናቸውን እንዲወጡ ጥሪ ቀረበ

You are currently viewing የጥምቀት በዓል ኃይማኖታዊና ትውፊታዊ እሴቱን ጠብቆ በድምቀት እንዲከበር ወጣቶች ሚናቸውን እንዲወጡ ጥሪ ቀረበ

AMN – ጥር 9/2017 ዓ.ም

‎የከተራ እና የጥምቀት በዓል ኃይማኖታዊና ትውፊታዊ እሴቱን ጠብቆ በድምቀት እንዲከበር ወጣቶች ሚናቸውን እንዲወጡ ጥሪ ቀርቧል።

‎የአዲስ አበባ ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ ከሸገር ከተማ ወጣቶች ጋር በበዓሉ አከባበር ዙሪያ መክሯል።

‎በምክክር ሂደቱ ላይ የተገኙት በብልጽግና ፓርቲ የአዲስ አበባ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ምክትል ሀላፊና የፖለቲካ ዘርፍ ሀላፊ አለማየሁ እጅጉ፣ ባለፉት ጊዜያት የተከበሩ የአደባባይ በዓላት በድምቀት ለመከበራቸው የአዲስ አበባና የሸገር ከተማ ወጣቶች አስተዋጽኦ የላቀ እንደነበር አንስተዋል።

የከተራና የጥምቀት በዓል በድምቀት እንዲከበር ይህንኑ የተለመደውን ተግባር ማከናወን ያስፈልጋል ብለዋል።

‎የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በዓሉ በድምቀት ይከበር ዘንድ ከሰው ሀይል በተጨማሪ በቴክኖሎጂ የታገዘ እንዲሆን አስፈላጊው ዝግጅት ተደርጓል ሲሉ ገልጸዋል።

‎የአዲስ አበባ ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ ኃላፊ አቶ በላይ ደጀን፣ የጥምቀት በዓል የአንድነታችን መገለጫ በዓል በመሆኑ ይህንን በዓል በድምቀት ለማክበር የወጣቶች ሚና ወሳኝ ነው ብለዋል።

‎የሸገር ከተማ አስተዳደር ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ ኃላፊ ናስር ሁሴን በበኩላቸው፣ የሁለቱ ከተማ ወጣቶች ኢትዮጵያዊ በሆነ የእንግዳ አቀባበል በዓሉ እሴቱን ጠብቆ እንዲከበር ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳላቸው ተናግረዋል፡፡

‎ወጣቶቹ በበኩላቸው በዓሉ ሀይማኖታዊና ባህላዊ እሴቱን ጠብቆ በድምቀት እንዲከበር እና በዓሉን ለማክበር የሚመጡ እንግዶችንም በተለመደው እንግዳ አቀባበል ለመቀበልና ለመሸኘት ተዘጋጅተናል ብለዋል።

በሄለን ጀንበሬ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review