AMN- ጥር 12/2017 ዓ.ም
የአየር ንብረት ለውጥ አሉታዊ ተፅዕኖን ለመቀነስ የአየር ትንበያን ማዘመንና የመረጃ ተደራሽነትን ማስፋት ላይ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን የኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ፈጠነ ተሾመ ገለጹ።
69ኛው የአፍሪካ ቀንድ የአየር ንብረት ትንበያ ፎረም በአዲስ አበባ እየተካሄደ ነው።
“የአየር ንብረት አገልግሎት፤ የቅድመ ማስጠንቀቂያ ክፍተቶችን በጋራ ለመሙላት” በሚል መሪ ሀሳብ የሚካሄደውን ፎረም የምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግስታት ባለስልጣን(ኢጋድ) የአየር ንብረት ትንበያ እና የመተግበሪያ ማዕከል ከልማት አጋሮች ጋር ያዘጋጁት ነው።
የኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ፈጠነ ተሾመ በፎረሙ መክፈቻ ላይ እንዳሉት የአየር ንብረት ለውጥ የአለም ፈተና ቢሆንም በቀጣናው እያደረሰ ያለው ተፅዕኖ ከፍተኛ ነው ብለዋል።

ተለዋዋጭ የሆነውን የአየር ንብረት ለውጥ አስቀድሞ ማወቅና መረጃን ተደራሽ ማድረግ ሊደርስ የሚችለውን አሉታዊ ተፅዕኖ መቀነስ የሚያስችል መሆኑንም ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥን ለመቋቋምና የአየር ትንበያ አገልግሎትን ለማዘመን በትኩረት እየሰራች ነው ብለዋል።
የምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግስታት ባለስልጣን(ኢጋድ) የአየር ንብረት ትንበያ እና የመተግበሪያ ማዕከል(ICPAC) ዳይሬክተር አብዲ ፊዳ (ዶ/ር) በበኩላቸው አለምን እየፈተነ ላለው የአየር ንብረት ለውጥ የተቀናጀና የተናበበ ምልሽ መስጠት ያስፈልጋል ብለዋል።
የምስራቅ አፍሪካ በአየር ንብረት ለውጡ ተደጋጋሚ ተፅዕኖ የሚደርስበት እንደመሆኑ ትንበያውን አስቀድሞ ማሳወቅ ይገባል ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
በፎረሙ እ.አ.አ ከመጋቢት እስከ ግንቦት 2025 ያለው ቀጣናዊ የአየር ትንበያ ይፋ ይደረጋል።
እ.አ.አ ከጥቅምት እስከ ህዳር 2024 የነበረው የአየር ንብረት ትንበያ አፈጻጸምም ውይይት ይደረግበታል ተብሏል።
ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር አቅም ለመገንባት በመተግበር ላይ ያሉ ስትራቴጂዎች እና የተገኙ ውጤቶች ላይ የተመለከተ ውይይትም እንደሚካሄድ ይጠበቃል ።
በፎረሙ የዘርፉ ተመራማሪዎች፣ ፖሊሲ አውጪዎችና የልማት አጋሮች ተገኝተዋል።