AMN – ጥር 13/2017 ዓ.ም
ተመራጩ የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ሀገራቸው ከዓለም ጤና ድርጅት እንድትወጣ የሚያደርገውን ‘ታላቁን’ የውሳኔ ሐሳብ በፊርማቸው አፅድቀዋል።
ፕሬዚዳንቱ ወደ ኋይት ሐውስ ከተመለሱ በኋላ በመጀመሪያው ቀን ከፈረሟቸው 200 ዶክመንቶች ውስጥ ይኼኛው እጅግ ግዙፍ ነው ተብሏል።
የመኖሪያ ፈቃድ የሌላቸው ስደተኞችን ከሀገራቸው ጠራርገው እንደሚያስወጡ የዛቱበት እና ወደ ቢሯቸው ከገቡ በኋላ በፊርማቸው ያፀደቁት ስደተኞችን የማስወጣት ውሳኔ ሌላኛው ግዙፉ ውሳኔ ነው።
ዶናልድ ትራምፕ አሜሪካ ከዓለም ጤና ድርጅት እንድትወጣ ሲያዙ ይኼኛው ለሁለተኛ ጊዜ ሲሆን አንደኛው ትዕዛዝ 45ኛውፕሬዝደንት በነበሩበት ወቅት የፈረሙት ነው።
ትራምፕ የዓለም አቀፉ ተቋም የኮቪድ-19 ወረርሽኝን የያዘበትን አግባብ ሲተቹ እንደነበር የሚታወስ ሲሆን በወረርሽኙ ወቅት ሀገራቸው ከድርጅቱ እንድትወጣ ሂደት ጀምረው ነበር። ይሁን እንጂ የቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዚዳንት የነበሩት ጆ ባይደን ውሳኔውን ቀልብሰው ቆይተዋል።
አዲሱ ፕሬዚዳንት ወደ ቢሯቸው እንደተመለሱ ሂደቱ እንዲጀምር የመጀመሪያው ውሳኔያቸው መሆኑ ታዲያ አሜሪካ በይፋ ከዓለም ጤና ድርጅት የምትወጣ መሆኑን አመላካች እንደሆነ የቢቢሲ ዘገባ አመልክቷል።
የውሳኔ ሐሳቡን ከፈረሙ በኋላ በኋይት ሐውስ የድርጅቱን ስም ጠቅሰው ባደረጉት ንግግር፣ “እኛ ወደ ተቋሙ እንድንመለስ አበከረው ይፈልጋሉ፣ እናም የሚፈጠረውን እናያለን” ሲሉ ምናልባት ወደፊት ሀገሪቱ የምትመለስበት ሁኔታ መኖሩን ጠቁመዋል።