ኢትዮጵያ ያላትን ምቹ የኢንቨስትመንት ሁኔታ ለጃፓን ባለሃብቶች የሚያስተዋውቅ ሴሚናር እየተካሄደ ነው

You are currently viewing ኢትዮጵያ ያላትን ምቹ የኢንቨስትመንት ሁኔታ ለጃፓን ባለሃብቶች የሚያስተዋውቅ ሴሚናር እየተካሄደ ነው

AMN- ጥር 14/2017 ዓ.ም

የኢትዮ ጃፓን የንግድና የኢንቨስትመንት ሴሚናር በአዲስ አበባ እየተካሄደ ሲሆን በሴሚናሩ ላይ ከ35 በላይ የጃፓን የቢዝነስ ልዑክ አባላት እየተሳተፉ ነው።

በሴሚናሩ ላይ የንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስትሩ ካሳሁን ጎፌ (ዶ/ር) ባደረጉት ንግግር መድረኩ የሁለቱን ሀገራት ግንኙነት የበለጠ የሚያጠናክር ነው ብለዋል።

ኢትዮጵያ በኢኮኖሚ ሪፎርም ስራዎቿ አበረታች ውጤት እያስመዘገበች መሆኑን ጠቅሰው ለ3 ቀናት የሚቆየው ሲምፖዚየም ለጃፓን ባለሃብቶች ኢትዮጵያ ለኢንቨስትመንት ያላትን ምቹ ሁኔታ ለማስተዋወቅ ሰፊ ዕድል የሚሰጥ ነው ብለዋል።

የኢፌዴሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ምስጋኑ አረጋ በበኩላቸው ሴሚናሩ የጃፓንን ቴክኖሎጂና የፈጠራ አቅም ለኢትዮጵያውያን ለማስተዋወቅና ኢትዮጵያም ለኢንቨስትመንት ያላትን ምቹ ሁኔታ ለጃፓናውያን ባለሃብቶች በአግባቡ ለማስተዋወቅ ዕድል እንደሚፈጥር ተናግረዋል።

በኢትዮጵያ የጃፓን አምባሳደር ሺባታ ሂሮኖሪ በኢትዮጵያ ያለው የኢንቨስትመንት ዕድልና የአገልግሎት አሰጣጥ የጃፓን ባለሃብቶችን የሚስብ በመሆኑ የሀገራቸው ባለሃብቶች በዚህ ዕድል እንዲጠቀሙ ጠይቀዋል።

በጃፓን የኢትዮጵያ አምባሳደር ዳባ ደበሌ በበኩላቸው ኢትዮጵያና ጃፓን ዘመናትን የተሻገረ ጠንካራ ወዳጅነት እንዳላቸው ጠቅሰው በትምህርት በከተማ ልማትና በማህበራዊ ግልጋሎት ጃፓን ለኢትዮጵያ ከፍተኛ ድጋፍ ስለማድረጓ ተናግረዋል።

በስካይላይት ሆቴል መካሄድ በጀመረውና ለ3 ቀናት በሚቆየው የንግድና ኢንቨስትመንት ሴሚናርም ከጃፓን 36 ኩባንያዎች ከኢትዮጵያ ደግሞ ከ100 በላይ ድርጅቶች እንደሚሳተፉ ተናግረዋል።

በምትኩ ተሾመ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review