AMN – ጥር 14/2017 ዓ.ም
በመርሀግብሩ ላይ የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት አስራት አፀደወይን (ዶ/ር) በጤና ባለሙያዎች ስልጠና ደረጃ መስከረም 24 ቀን 1947 ዓ.ም የተመሰረተው የጎንደር ዩኒቨርሲቲ በሰባት አስርት ዓመታት ውስጥ ከሀገር አልፎ በዓለም አቀፍ ደረጃ ብቁ ሙያተኞችን በማፍራት ግንባር ቀደም ነው ብለዋል፡፡
በችግር ፈቺ የምርምር ስራዎቹ ምሳሌ መሆን የቻለ የትምህርት ተቋም መሆን ችሏልም ብለዋል።
በተለይም ዩኒቨርሲቲው በህክምና ትምህርትና አገልግሎት ዘርፍ በዓለም አቀፍ ደረጃ ጉልህ አበርክቶ ያለው ተመራጭ የከፍተኛ ትምህርት ተቋም ነውም ብለውታል ፕሬዚዳንቱ።
የጎንደር ዩኒቨርሲቱ አሁን ለደረሰበት ደረጃም ከቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ጀምሮ መሪዎች ላደረጉለት እና እያደረጉለትም ላለው ያልነጠፈ ድጋፍ በዩኒቨርሲቲው ስም ምስጋና አቅርበዋል።
የትምህርት ሚኒስትሩ ብርሀኑ ነጋ (ፕ/ር) ባለፉት አስርት ዓመታት በኢትዮጵያ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማትን ተደራሽነት ለማስፋት ሰፊ ጥረት ሲደረግ እንደነበር አውስተዋል።
ተደራሽነቱን ያህል ግን ለትምህርት ጥራት ተሰጥቶት የነበረው ትኩረት አናሳ መሆኑ በትምህርት ስርዓቱ ላይ አሉታዊ ጫና ሲያሳድር ቆይቷልም ብለዋል።
በመሆኑም የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ ሰፊ ጥረት እየተደረገ ተከታታይ ርምጃዎችም እየተወሰዱ ይገኛሉ ብለዋል።
የከፍተኛ ትምህርት ተቋማትን አቅም በማጎልበት ዓለም አቀፍ ይዘት እንዲኖራቸው እየተሰራ ይገኛልም ነው ያሉት የትምህርት ሚኒስትሩ።
በዚህ ረገድ የትምህርት ተቋማቱ ራስ ገዝ እንዲሆኑ የማድረግ ተልዕኮን የጠቀሱት ሚኒስትሩ በመጪዎቹ ሁለት ዓመታት ውስጥ የራስ ገዝ ዩኒቨርሲቲዎችን ቁጥር ወደ 10 ለማሳደግ ዕቅድ ተይዟልም ብለዋል።
ሚኒስትሩ የጎንደር ዩኒቨርሲቲ በትምህርት ፣ምርምርና ማህበረሰብ አገልግሎት ጉልህ አበርክቶ ያለው የትምህርት ተቋም መሆኑን አንስተዋል።
ዩኒቨርሲቲው ዓለም ከደረሰበት ደረጃ ሀገራዊ ዘላቂ ልማትን ማረጋገጥ የሚችል ተቋም ሆኖ እንዲቀጥል የጀመራቸውን ጥረቶች አጠናክሮ እንዲቀጥልም ሚኒስትሩ ጥሪ አቅርበዋል።
የጎንደር ዩኒቨርሲቲ 70ኛ ዓመት እንዲሁም የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ኮምፕረሄንሲቭ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል 100ኛ ዓመት የምስረታ በዓል እስከ ሰኔ 30 ድረስ የሚቀጥል መሆኑ ተነግሯል።
በአቡ ቻሌ