AMN-ጥር 15/2017 ዓ.ም
በስራ መግቢያ እና መውጪያ ሰዓት ላይ የሚታየውን የመንግሥት ሰራተኞች አውቶቢስ እጥረት ለማሻሻል ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ መሆኑን የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስቴር አስታውቋል፡፡
የፐብሊክ ሰርቪስ ትራንስፖርት አገልግሎት ድርጅት ከቁልፍ ባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት መስራት የሚያስችለውን የምክክር መድረክ አካሄዷል።
በመድረኩ ላይ የተገኙት የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስትር ዴኤታ በርሆ ሀሰን፣ በፐብሊክ ሰርቪስ ትራንስፖርት አገልግሎት የተፈጠረው መጨናነቅ መንስዔው ባለፉት ሶስት ዓመታት አውቶቢሶችን ለመግዛት ታቅዶ መግዛት ባለመቻሉ መሆኑን በማንሳት የፐብሊክ አውቶቢስ ተደራሽነት ጥያቄን ለመመለስ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
የፐብሊክ ሰርቪስ ትራንስፖርት አገልግሎት ድርጅት ዋና ዳይሬክተር አቶ ጥላሁን ጅግሶ በበኩላቸው፣ በመንግስት ሠራተኛው ትራንስፖርት ዘርፍ በአገልግሎት አሰጣጥ የታየውን መጨናነቅ ለመቀነስ አገልግሎቱ እጅግ ዘመናዊና ለረዥም ጉዞ የሚሆኑ ልዩ አገር አቋራጭ አውቶቢሶችን በጊዜያዊነት ወደ አገልግሎት በመመለስ ማስተካከያ በማድረግ ላይ እንደሚገኝ ገልፀዋል።
በተጨማሪም የፐብሊክ ትራንስፖርት አገልግሎት ድርጅት የከተማዋን የትራንስፖርት እጥረት ለማቃለል በሚደረገው ርብርብ የበኩሉን ድጋፍ እያደረገ እንደሚገኝ ጠቁመዋል፡፡
በዚህም ከስራ መግቢያና መውጫ ሰዓት ውጪ 320 አውቶብሶችን ለህዝብ ትራንስፖርት አገልግሎት በየቀኑ በማሰማራት እንዲሁም 47 አውቶብሶችን ለልዩ ሀገር አቋራጭ ትራንስፖርት በመመደብ ህብረተሰቡን በማገልገል ላይ እንደሚገኝ ተመላክቷል፡፡
በአሸናፊ በላይ