የጉምሩክ ኮሚሽን አገልግሎት አሰጣጡን ለማዘመን እና የህግ ተገዥነትን ለማረጋገጥ የሚያስችሉ የተለያዩ የቴክኖሎጂ ውጤቶችን ተግባራዊ እያደረገ ነው፡-ኮሚሽነር ደበሌ ቃበታ

You are currently viewing የጉምሩክ ኮሚሽን አገልግሎት አሰጣጡን ለማዘመን እና የህግ ተገዥነትን ለማረጋገጥ የሚያስችሉ የተለያዩ የቴክኖሎጂ ውጤቶችን ተግባራዊ እያደረገ ነው፡-ኮሚሽነር ደበሌ ቃበታ

AMN – ጥር 16/2017 ዓ.ም

የጉምሩክ ኮሚሽን አገልግሎት አሰጣጡን ለማዘመን እና የህግ ተገዥነትን ለማረጋገጥ የሚያስችሉ የተለያዩ የቴክኖሎጂ ውጤቶችን ተግባራዊ እያደረገ መሆኑን የጉምሩክ ኮሚሽን ኮሚሽነር ደበሌ ቃበታ ገለጹ፡፡

ኮሚሽኑ የኤሌክትሮኒክ ካርጎ ትራኪንግ ስርዓት፣ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስን መሰረት ያደረገ የድንበር ቁጥጥር እንዲሁም ሌሎች የቴክኖሎጂ ውጤቶች ልማት ያለበት ደረጃ እና ወደ ሙሉ ትግበራ በሚገባበት ሁኔታ ላይ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ውይይት አድርጓል፡፡

በውይይቱ የጉምሩክ ኮሚሽን ኮሚሽነር ደበሌ ቃበታ፣ የአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ወርቁ ጋቸና (ዶ/ር)፣ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የፕሮጀክቶቹ ስራ አስኪያጅ ሽብሩ ተመስገን (ዶ/ር) እና ሌሎች የኮሚሽኑ አመራሮች ተገኝተዋል፡፡

የጉምሩክ ኮሚሽን ኮሚሽነር ደበሌ ቃበታ፣ የኮሚሽኑን አገልግሎት አሰጣጥ ለማዘመን እና የህግ ተገዥነትን ለማረጋገጥ የሚያስችሉ የተለያዩ የቴክኖሎጂ ውጤቶች ተግባራዊ እየተደረጉ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ከአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስትትዩት እና ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመቀናጀት ኤሌክትሮኒክ ካርጎ ትራኪንግ ስርዓት እና ሌሎች ቴክኖሎጂዎችን ወደ ሙሉ ትግበራ ለማሸጋገር እየተሰራ መሆኑንም ኮሚሽነሩ አስረድተዋል፡፡

የአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ወርቁ ጋቸና (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ ኢንስቲትዩቱ የኮሚሽኑን አገልግሎት የሚያሳልጡ ዘርፈ ብዙ የቴክኖሎጂ ውጤቶችን እያለማ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

የኢትዮጵያ ኤሌክትሮኒክ ካርጎ ትራኪንግ ስርዓት እና ሌሎች ቴክኖሎጂዎችን ወደ ሙሉ ትግበራ ለማሸጋገርም ከፍተኛ ርብርብ እየተደረገ ነው ብለዋል፡፡

በውይይቱ የኢትዮጵያ ኤሌክትሮኒክ ካርጎ ትራኪንግ ስርዓት እና ሌሎች ቴክኖሎጂዎች ያሉበት ደረጃ በዝርዝር የተገመገመ ሲሆን ቀሪ ስራዎች በአጭር ጊዜ ተጠናቀው ወደ ሙሉ ትግበራ እንዲገቡ አቅጣጫ መቀመጡን ከኮሚሽኑ የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review