የኢትዮጵያ ሆስፒታሎች ጥምረት ለጥራት ፕሮግራም የሆስፒታሎችን አገልግሎት አሰጣጥ ለማሻሻል ጠቃሚ ነው -ዶክተር መቅደስ ዳባ

You are currently viewing የኢትዮጵያ ሆስፒታሎች ጥምረት ለጥራት ፕሮግራም የሆስፒታሎችን አገልግሎት አሰጣጥ ለማሻሻል ጠቃሚ ነው -ዶክተር መቅደስ ዳባ

AMN-ጥር 18/2017 ዓ.ም

የጤና ሚኒስቴር ያዘጋጀው አገር አቀፍ የኢትዮጵያ ሆስፒታሎች ጥምረት ለጥራት ፕሮግራም የስድስት ወራት አፈጻጸም የግምገማ መድረክ በአዳማ ከተማ ተካሂዷል።

የጤና ሚኒስትር ዶ/ር መቅደስ ዳባ፣ እንደ ሀገር ጠንካራ የጤና ሥርዓት በመገንባት የአገልግሎት ጥራትን ማረጋገጥ ያስፈልጋል ብለዋል፡፡

የማህበረሰቡን የጤና አገልግሎት ፍላጎት ለማሻሻልና የሆስፒታሎችን የአገልግሎት አሰጣጥ ለማሻሻል የኢትዮጵያ ሆስፒታሎች ጥምረት ለጥራት ፕሮግራም ጉልህ አስተዋጽኦ አድርጓል ሲሉም ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ሆስፒታሎች ጥምረት ለጥራት ፕሮግራም መርሃ ግብር ከ2004 ዓ.ም ጀምሮ ተቀርፆ 4ኛው ምዕራፍ ድረስ በሁሉም ክልሎች ተግባራዊ እየተደረገ መሆኑን ጠቅሰው ፕሮግራሙ በሆስፒታሎች መካከል ጠንካራ ትስስርና መደጋገፍን በመፍጠር የህብረተሰቡን የህክምና የአገልግሎት ፍላጎት እርካታ ለማሳደግ ምቹ አሰራርን እንደፈጠረ ተናግረዋል።

ፕሮግራሙ እንደ ሀገር ያለውን የሰው ሀይልና የህክምና መሳሪያዎች በጋራ በመጠቀም የማህበረሰቡን የአገልግሎት ፍላጎት በከፍተኛ ደረጃ እንዳሻሻለው ጠቁመዋል፡፡

የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ዶ/ር ደረጀ ዱጉማ በበኩላቸው፤ ጤና ተቋማት የማህበረሰቡን የአገልግሎት ፍላጎትና እርካታ በተጨባጭ ለማረጋገጥ ውጤታማ የሆነ ስራዎችን መስራት እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል፡፡

የህክምና አገልግሎት ተደራሽነትንና ጥራትን ለማረጋገጥ የዘርፉን የህክምና ግብዓትና መሠረተ ልማት ለማሟላት ሚኒስቴር መ/ቤቱ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑን መግለጻቸውን የጤና ሚኒስቴር መረጃ ያሳያል።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review