AMN – ጥር- 18/2017 ዓ.ም
በጥቂት ዓመታት ውስጥ የሀገርን ወጪ በራስ የገቢ አቅም መሸፈን የሚችል ጠንካራ የኢኮኖሚ ሥርዓት ለመገንባት በትኩረት እየተሰራ መሆኑን የብልፅግና ፓርቲ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባል እና የገቢዎች ሚኒስትር አይናለም ንጉሴ ገለጹ።
የገቢዎች ሚኒስትሯ ወይዘሮ አይናለም ንጉሴ ሀገራዊ ለውጡን ተከትሎ የተወሰዱ የማሻሻያ ዕርምጃዎች በገቢ አሰባሰብና አስተዳደር ሥርዓቱ ላይ የተመዘገቡ ስኬቶችን በማስመልከት ማብራሪያ ሰጥተዋል።
የብልፅግና ፓርቲ አፍሪካዊት የብልፅግና ተምሳሌት ኢትዮጵያን ለመገንባት በሰጠው ትኩረት በገቢ ዘርፉ በ2022 የሀገርን ወጪ በራስ አቅም የመሸፈን ርዕይ ሰንቆ እየሰራ ነው ብለዋል።
በመጀመሪያው የብልፅግና ፓርቲ ጉባኤ ከተቀመጡ አጀንዳዎች መካከል ጠንካራና ጫናን የሚቋቋም ኢኮኖሚ ለመገንባት የሀገር ውስጥ ገቢ አቅምን ማሳደግ አንዱ መሆኑንም ጠቅሰዋል።
በዚህም ከሀገራዊ ለውጡ በፊት ከ2 ቢሊየን ብር በታች በነበረው ዝቅተኛ የገቢ አሰባሰብ ሥርዓት በተወሰደ ማሻሻያ እርምጃ እመርታዊ ለውጥ እየተመዘገበ መሆኑን አስታውቀዋል።
በተደረጉ ማሻሻያዎችም በ2014 ዓ.ም 336 ቢሊየን ብር፣ በ2015 ዓ.ም 442 ቢሊየን ብር እና በ2016 ዓ.ም 512 ቢሊየን ብር በመሰብሰብ የገቢ ዕድገት እየተመዘገበ መምጣቱን አብራርተዋል።
የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ተዋናዮች የሚከፍሉት የገቢ ግብርም ዜጎች በጋራ የሚጠቀሙባቸው የጋራ መሰረተ ልማቶችን በፍትሕዊነት ለመገንባት አዎንታዊ ሚና እየተወጡ መሆናቸውን ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ የተሟላ ሀገራዊ የኢኮኖሚ ማሻሻያም ዘመናዊና ተወዳዳሪ የኢንቨስትመንት ሥርዓትን በመፍጠር የገቢ አቅምን ለማሻሻል ትልቅ አቅም እንደሆነ ተናግረዋል።
የኢትዮጵያን ወጪ በራሷ ገቢ መሸፈን የሚችል ጠንካራ ኢኮኖሚ ሥርዓት ለመገንባት በትኩረት እየተሰራ እንደሚገኝም ገልጸዋል።
በተያዘው በጀት ዓመትም ከሀገር ውስጥና ከውጭ ቀረጥና ታክስ 900 ቢሊየን ብር ገቢ ለመሰብሰብ ታቅዶ እየተሰራ መሆኑን የገለጹት ሚኒስትሯ፤ ባለፉት ስድስት ወራትም 451 ቢሊየን ብር ገቢ መሰብስብ መቻሉን ተናግረዋል።
በአጠቃላይ በገቢ አሰባሰብ ሥርዓቱ በብልፅግና ፓርቲ መሪነት የተቀመጠውን ርዕይ ማሳካት የሚያስችል ስኬታማ ስራ እየተከናወነ እንደሚገኝ አስረድተዋል።
በኢትዮጵያ የታክስና ጉምሩክ አስተዳደር ሕግጋት መነሻነት ዜጎች በሚያመነጩት ገቢ ልክ ግብርን በታማኝነት በመክፈል ሀገራዊ ግዴታቸውን መወጣት የሚያስችሉ ሰፋፊ ስራዎች መሰራታቸውንም ገልጸዋል።
የግብር ከፋዮች ታክስን የማሳወቅ ልምምድ እያደገ ነው ያሉት ሚኒስትሯ፤ በግብር ከፋዩና ተቋሙ መካከል የሚስተዋልን የሒሳብ ልዩነት ለማጥበብ የሚሰጠው ትምህርትና ስልጠና ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።
ሀገራዊና ዓለም አቀፋዊ ሁኔታን የሚገነዘብ የሰው ሃይል በመገንባት በዲጂታል ኢትዮጵያ ርዕይ ስር ግብር ከፋዮች በዘመናዊ የክፍያ ሥርዓት ያለእንግልት በኦላይን የሚከፍሉበት ዕድል መፈጠሩን ተናግረዋል።
በዚህም በ2013 ዓ.ም 5 ሺህ 901 የኦላይን ግብር ከፋይ ከነበረበት በ2016 ዓ.ም በጀት ዓመት 48ሺህ 349 ግብር ከፋዮች በኦላይን ማሳወቅ የቻሉበት አቅም እንደተፈጠረ መግለፃቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
በብዝኅ የኢኮኖሚ ሥርዓት ለግብርና፣ ማዕድን፣ አይ.ሲ.ቲ፣ ኢንዱስትሪና ቱሪዝም የተሰጠው ትኩረት የገቢ አቅምን በማሳደግ ቀጣይነት ያለው ሀገራዊ የኢኮኖሚ ዕድገት እንዲመዘገብ ማስቻሉንም አንስተዋል።