AMN – ጥር- 18/2017 ዓ.ም
ብልፅግና ፓርቲ ሁሉም ብሔር ብሔረሰቦች በአገሪቱ እኩል የፖለቲካ ተሳትፎ እንዲኖራቸው በማድረግ የማህበረሰቡን ተጠቃሚነት እያረጋገጠ መሆኑን የሀረሪ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኦርዲን በድሪ ገለፁ።
የብልፅግና ፓርቲ የኢትዮጵያን የፖለቲካ ስብራት በመጠገን የህዝቦችን ጥያቄዎች ለመመለስ እያከናወናቸው የሚገኙ ተግባራት ተጨባጭ ውጤቶችን እያስመዘገቡ እንደሚገኙ የሀረሪ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኦርዲን በድሪ ገልፀዋል።
በተለይ ፓርቲው ዋናና አጋር በሚል ቀድሞ የነበረውን አደረጃጀት በማስቀረት ሁሉም ብሄር ብሄረሰቦች ውክልና ኖሯቸው እኩል ተሳታፊ እና ተጠቃሚ እንዲሆኑ ማስቻሉን አስገንዝበዋል።
ፓርቲው የልዩነት ግንቦችን በመናድ፣ በሀሳብ ትግል ብቻ የተመሰረተ ፖለቲካዊ እንቅስቃሴ እውን እንዲሆን በማድረግ ቀድሞ የነበረውን የሴራ ፖለቲካ ወደ መርህ ፖለቲካ በመቀየር የመገፋፋት እና ጥላቻ ፓለቲካን ወደ ሰላምና አብሮነት የቀየረ መሆኑንም ጠቁመዋል።
በዚህም ፓርቲው በአካታችነቱ እና ሰው ተኮር የልማት ስራዎቹ ቅቡልነትን በማግኘቱ በኢኮኖሚ፣ ማህበራዊና ፖለቲካዊ ዘርፎች በአገሪቱ ብሎም በሀረሪ ክልል ታላላቅ ስኬቶችን ማስመዝገብ የቻለ መሆኑን አስረድተዋል።
በተለይ በክልሉ በኢኮኖሚው መስክ በቱሪዝም እና በግብርና ልማት የክልሉን ህዝብ ተጠቃሚ ለማድረግ በተከናወኑ ተግባራት ተጨባጭ ውጤቶች መመዝገባቸውን ጠቅሰዋል።
በማህበራዊ ልማት ዘርፍም የትምህርት ጥራት ተደራሽነትን እና የጤና አገልግሎት ተደራሽነትን ከማረጋገጥ አንጻር የተለያዩ ስራዎች ማከናወን መቻሉን ርዕሰ መስተዳድሩ አክለዋል።
በቀጣይም በሁሉም ዘርፎች የተመዘገቡ አበረታች ስኬቶችን በውጤት አጅቦ ለማስቀጠል በትኩረት እንደሚሰራ መግለፃቸውን ኢዜአ ዘግቧል።