AMN – ጥር 19/2017 ዓ.ም
በ2016/17 የምርት ዘመን 905 ሚሊየን ኩንታል ሰብልና የሆርቲካልቸር ምርት ማግኘት መቻሉን ግብርና ሚኒስቴር የግብርና ሚኒስትር ግርማ አመንቴ (ዶ/ር) ተናገሩ፡፡
6ኛው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 4ኛ ዓመት የስራ ዘመን 1ኛ ልዩ ስብሰባ እየተካሄደ ነው፡፡
በልዩ ስብሰባው የግብርና ሚኒስትር ግርማ አመንቴ (ዶ/ር) ለምክር ቤቱ የሚኒስቴሩን የ2017 በጀት ዓመት የ6 ወራት የዕቅድ አፈጻጸም ሪፖርት አቅርበዋል፡፡
በ2016/17 የምርት ዘመን በሰብል፤ በሆርቲካልቸር እና ጥጥ ልማት 30 ነጥብ 9 ሚሊየን ሄክታር መሬት ማልማት መቻሉን ያነሱት ሚኒስትሩ እስከ አሁን ከተሰበሰበው 19 ነጥብ 9 ሚሊየን ሄክታር መሬት 905 ሚሊየን ኩንታል የሰብልና የሆርቲካልቸር ምርት ማግኘት እንደተቻለ ጠቅሰዋል፡፡
ግብርና የሀገሪቱ የኢኮኖሚ ዋልታ ሆኖ የቆየ እና አሁንም በማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ልማት ውስጥ ጉልህ ሚና እየተጫወተ ያለ ዘርፍ መሆኑን ሚኒስትሩ በሪፖርታቸው አንስተዋል ፡፡
የግብርና ዘርፍ ተከታታይነት ያለው እድገት እያሳየ የመጣ መሆኑን እና በገጠር ያለውን ድህንት እንዲቀንስ ማስቻሉን ተናግረዋል፡፡
ዘርፉ የሌሎች ዘርፎችን ልማት በማገዝ ለአጠቃላይ ኢኮኖሚያዊ እድገት ከፍተኛውን ድርሻ በማበርከት የመሪነት ሚናውን እየተጫወተ እንደሚገኝም ገልጸዋል፡፡
በአሁኑ ወቅት ሁሉንም የግብርና ወቅቶች ማለትም የበልግ፣ የመኸር እና የበጋ መስኖን በአግባቡ በመጠቀም የሰብል እና የሆርቲካልቸር ሥራዎች እየተሰሩ እንደሚገኙም አመላክተዋል፡፡
በዚህም መሠረት አሁን ላይ ዓመት በአነስተኛ ይዞታ የአርሶ አደር ፤በመካከለኛ እና ሰፋፊ እርሻዎች በሁሉም የምርት ወቅቶች በሰብል፣ በሆርቲካልቸር እና ጥጥ ልማት በአጠቃላይ 30 ነጥብ 6 ሚሊየን ሄክታር መሬት ለማልማት እና 1 ነጥብ 4 ቢሊየን ኩንታል ምርት ለማምረት ታቅዶ እየተሰራ እንደሚገኝም ጠቁመዋል፡፡
የአሥር ዓመቱን መሪ ዕቅድ መሠረት አድርጎ የተቀረፀው የሦስት ዓመት መካከለኛ ዘመን ዕቅድ የግብርና አጠቃላይ ዓመታዊ ዕቅድ በ6 በመቶ ለማሳደግ ግብ ተቀምጦ ለአፈፃጸሙ ስኬታማነት ርብርብ እየተደረገ እንደሚገኝም ገልጸዋል፡፡
በመጀመሪያው መካከለኛ ዘመን በ2016 በጀት ዓመት የተመዘገበወ እድገት 6 ነጥብ 9 በመቶ ሲሆን፣ ባለፉት ዓመታት ያጋጠሙ ተግዳሮቶችን በመቋቋም ይህ እድገት እንዲመዘገብ አስተዋጽዖ ላበረከቱ አርሶ አደሮች፣ ባለሙያዎች እና አመራሩ ምስጋና አቅርበዋል፡፡
በተያዘው በጀት ዓመት ተቋማዊ የአፈፃጸም አቅምን በማሳደግ፣ ከክልሎች ጋር በጋራ በማቀድ፣ ዕቅዱንም ተግባራዊ የማድረግ እና ተግባሩን የመከታተል ስራ እየተሻሻለ መምጣቱንም አመላክተዋል፡፡
የግብርና ዕድገትን ለማፋጠን እና ቀጣይነቱን ለማረጋገጥ አሰራሩን የማዘመን ሥራ እየተሰራ እንደሚገኝም ነው የገለጹት፡፡
በሰብል ልማት ሀገራችን ያሳካችው ውጤት የሀገራችንን ታሪክ የቀየረ እና በተለይም በስንዴ ፍላጎት በማሟላት ወደ ውጭ በመላክ አዲስ ታሪክ የተመዘገበ መሆኑንም አብራርተዋል፡፡
በታምራት ቢሻው