AMN – ጥር 22/2017 ዓ.ም
አዲስ አበባ በለውጡ ጊዜያት እያሳየች ያለችው እመርታ ለክልሎች አስተማሪ ነው ሲሉ ከነገ ጀምሮ በሚካሄደው የብልጽግና ፓርቲ 2ኛ ጉባኤ ላይ ለመሳተፍ የመጡት የብልጽግና ፓርቲ ስራ አስፈጻሚ አባላት ገለጹ፡፡
ከኢትዮጵያ የተለያዩ ክልሎች የተወጣጡ የብልጽግና ፓርቲ ስራ አስፈጻሚዎች በአዲስ አበባ የተለያዩ ሰው ተኮር ስራዎችን እየጎበኙ ነው፡፡
በአስራ አንድ ቡድን ተዋቅሮ ጉብኝት እያደረገ የሚገኘው የስራ አስፈጻሚ አባላት ጉብኝት የብልጽግና ፓርቲ ሰው ተኮር ስራዎች አካል የሆነውን የለሚኩራ የተቀናጀ የግብርና ምርት ማከፋፈያ የገበያ ማዕከል የመጀመሪያ ምልከታውን አድርጓል።
ጉብኝቱ የለሚ እንጀራ ማእከል፣በለሚኩራ ክፍለከተማ በበጎ ፈቃደኞች የተገነቡ የጋራ መኖሪያ ቤቶችና አዲስ ኮንቬንሽን ሴንተርን ያካተተ ሲሆን ጎብኚዎቹ ባዩት ነገር መደሰታቸውን ገልጸዋል።
ከተለያዩ ክልሎች የሚላኩ ምርቶችን ለተጠቃሚዎች በተመጣጣኝ ዋጋ ከማከፋፈል በተጨማሪ አምራች ሃይሉን ተጠቃሚ ማድረግን ታላሚ ያደረገው የለሚ ኩራ ገበያ ማዕከል የምርት አቅርቦት ችግርን በመቅረፍ ረገድ አይነተኛ ሚና እየተጫወተ እንደሆነም ተገልጿል።
ከነገ ጀምሮ በሚካሄደው የብልጽግና ፓርቲ ጉባኤ ላይ ለመሳተፍ የመጡት የፓርቲው አባላት አዲስ አበባ በለውጡ ጊዚያት እያሳየች ያለችው እምርታ ለክልሎች አስተማሪ እንደሆነ አውስተዋል።
የለሚኩራ ገበያ ማዕከልን የመጀመሪያ ጉብኝት ያደረገው ቡድን በጋምቤላ ክልል ፕሬዚዳንት አለሚቱ ኡሙድ የሚመራ ሲሆን የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስቴር ለገሰ ቱሉን ጨምሮ የተለያዩ ክልሎች ከፍተኛ አመራሮችም ተሳትፈዋል።
በአፈወርቅ ውበቱ