AMN – ጥር 22/2017 ዓ.ም
የኢትዮጵያ መንግሥት እና መሪው ብልጽግና ፓርቲ ለቀጣናው ሰላምና ብልጽግና ከሩዋንዳ ጋር ያላቸውን ትብብር አጠናክረው እንደሚቀጥሉ በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ማስተባበሪያ ማዕከል ሃላፊና የብልጽግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዝዳንት አደም ፋራህ ገለጹ።
አቶ አደም ፋራህ በሁለተኛው የብልጽግና ፓርቲ መደበኛ ጉባኤ ለመታደም ትላንት ምሽት አዲስ አበባ ከገቡት የሩዋንዳ አርበኞች ግንባር ፓርቲ ዋና ፀሐፊ ዌላርስ ጋሳማጌራን በጽህፈት ቤታቸው ተቀብለው አነጋግረዋል።
የሩዋንዳ አርበኞች ግንባር ፓርቲ ባለፈው ሐምሌ በተካሄደው ሀገራዊ ምርጫ የህዝቡን ድምጽና ይሁንታ አግኝቶ በማሸነፉ ደስታቸውን ገልጸውላቸዋል።
ብልጽግና ፓርቲ ለሰላምና ኢኮኖሚ ልማት ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ ነው ያሉት አቶ አደም፥ በመጀመሪያው ጉባኤ ለህዝብ የገባውን ቃል በተግባር አሳይቷል ብለዋል።
ኢትዮጵያ በፈጣን የኢኮኖሚ እድገት ላይ መሆኗንም አቶ አደም ገልጸዋል።
ፓርቲው በመጀመሪያ ጉባኤው ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ ባስቀመጠው አቅጣጫ መሰረት በስንዴ፣ በአትክልትና ፍራፍሬ፣ በሩዝና ሌሎች ምርቶችም እድገት መመዝገቡን ተናግረዋል።
በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) አነሳሽነት በአዲስ አበባ የተጀመረው የኮሪደር ልማት አሁን ላይ ከ50 በላይ ከተሞች ላይ እየተተገበረ መሆኑን ገልጸው፥ የገጠር ኮሪደር ልማትም መጀመሩን ጠቅሰዋል።
መንግሥት ለግብርና፣ ለቱሪዝም፣ ለኢንዱስትሪ፣ ለማዕድንና ለዲጅታል ዘርፎች ልዩ ትኩረት ሰጥቶ የዜጎችን የልማት ጥያቄ እየመለሰ መሆኑንም አንስተዋል።
ፓርቲው ሰላምና ብልጽግናን ቀዳሚ ትኩረቱ አድርጎ እየሠራ ነው ያሉት አቶ አደም፤ ከሩዋንዳ በፓርቲ ለፓርቲና መንግሥት ለመንግሥት ትብብር እየተሠራ ነው ብለዋል።
ኢትዮጵያና ሩዋንዳ ለሁለትዮሽ ለቀጣናዊና አህጉራዊ ሰላምና ብልጽግና በጋራ መስራታቸውን አጠናክረው ይቀጥላሉ ነው ያሉት።
የሩዋንዳ አርበኞች ግንባር ፓርቲ ዋና ፀሐፊ ዌላርስ ጋሳማጌራ በበኩላቸው ኢትዮጵያ በአስደናቂ የለውጥ ጉዞ ላይ መሆኗን አንስተው፥ ለተደረገላቸው ደማቅ አቀባበል ምስጋና አቅርበዋል።
ሩዋንዳ ከነበረችበት ውስብስብ ችግር በመውጣት ሰፋፊ የመልሶ ግንባታና የልማት ሥራዎችን በመተግበር ህዝብን ተጠቃሚ ያደረጉ ስኬቶችን ማስመዝገቧን ተናግረዋል።
ብልጽግና ፓርቲ ኢትዮጵያን ከፍ የሚያደርጉና የህዝብን ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ ተግባራትን በመፈጸም እያስመዘገበ ያለውን ስኬትም ዋና ፀሐፊው አድንቀዋል።
ሁለቱ ሀገራት በፓርቲ ለፓርቲና መንግሥት ለመንግሥት በበርካታ መስኮች ትብብራቸውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉም አረጋግጠዋል።
ለብልጽግና ፓርቲ ሁለተኛ መደበኛ ጉባኤ መልካም ምኞታቸውን መግለጻቸውን ኢዜአ ዘግቧል ።