ወሳኙ ጉባኤ በታላቁ ታሪክ መታሰቢያ

You are currently viewing ወሳኙ ጉባኤ በታላቁ ታሪክ መታሰቢያ

ጉባኤው የጋራ ትርክትን የመገንባት ግዙፍ አቅም በሆነው የዓድዋ ድል መታሰቢያ መደረጉ ትልቅ ትርጉም እንዳለው ምሁራኑ ተናግረዋል

ዓድዋ የኢትዮጵያውያን የታሪክ አንጓ ነው፡፡ ማማ ነው፤ ኢትዮጵያዊያኑ አብሮነታቸውን፣ ጀግንነታቸውን፣ ችግርን በውይይት የጋራ ጠላትን ደግሞ በህብረት ማሸነፍን ያስመሰከሩበት የፍትሕ አደባባይ ነው – ዓድዋ፡፡ ይህንን ታላቅ የታሪክ አብነት የሚመሰክረው የዓድዋ ድል መታሰቢያ ደግሞ በጋራ መቆምን፣ ማቀድንና መተግበርን የሚያስተምር ህያው ሐውልት ነው ሲሉ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ፎክሎርና የባህል ጥናት መምህር ታደሰ ጃለታ ይናገራሉ፡፡

ዓድዋ በወቅቱ የነበረው የኢትዮጵያ ህዝብ በአንድነት በመቆሙ ያስመዘገበው ድል ነው የሚሉት መምህር ታደሰ፣ ይህ ድል ሕብረ ብሔራዊነት የተገለጠበት የታሪክ አጋጣሚ ነበር፡፡ የዛሬው ትውልድም ከተባበረ ከዚህ የበለጠ ድል በአንድነት ማስመዝገብ ይችላል ብለዋል። አክለውም፣ የዛሬው ትውልድ ከጥቃቅን ጉዳዮች ወጥቶ እንደ ዓድዋ ድል ከፍ ባሉት ሀሳቦች ላይ አንድ መሆን አለበት። የዓድዋ ድል ከምንም በላይ መላው የኢትዮጵያ ህዝብ በቁርጠኝነት ቆሞ የባሪያነት ቀንበርን የታገለበትና ድል የነሳበት ገድል ስለመሆኑም አውስተዋል።

እንደ መምህር ታደሰ ገለፃ፣ አሁን ያለንበት ድህነት፤ ጉስቁልና እና አለመግባባት ከዚህ ቀደም በዓድዋ ላይ ከገጠመን ችግር የሚበልጥ አይደለም። ዛሬ እያጋጠመን ላለው ችግር በመደማመጥና በመነጋገር የማይፈታ ነገር ስለማይኖር አባቶች ያሳለፉትን ያንን ትልቅ ውጣ ውረድ መለስ ብሎ በመመልከት ትውልዱ ለሌላ ድል ራሱን ማዘጋጀት  እንዳለበትም መክረዋል፡፡

ዛሬ ደግሞ ታላቋን ሀገር እየመራ ያለው ብልፅግና ፓርቲ የዓድዋ ድልን ለመዘከር በተገነባው ታሪካዊ ስፍራ ወሳኙን ጉባኤ እያደረገ ነው፡፡ 2ኛው የብልጽግና ፓርቲ ጉባኤ ከጥር 23 እስከ 25 ቀን 2017 ዓ.ም የሚቆይ ሲሆን፣ “ከቃል እስከ ባህል” የሚል መሪ ቃል ተሰጥቶታል፡፡ በዚህ ጉባኤ ከ 1 ሺህ 7 መቶ በላይ ተሳታፊዎች እንደሚገኙ ተገልጿል።

የተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ተወካዮች፣ የውጭ ሀገራት ወዳጅ ፓርቲዎች ተወካዮች እና ሌሎች ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች እንደሚገኙም ተነግሯል። የብልፅግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዝዳንት እና ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ አደም ፋራህ ጉባኤውን አስመልክቶ በሰጡት መግለጫ፣ በአንደኛው የፓርቲው ጉባኤ ቃል የተገቡ ስራዎችን በመገምገም በቀጣይም ፓርቲው የሚፈፅማቸውን እቅዶች፣ ያስቀመጣቸውን አቅጣጫዎች እና ትልልቅ ውሳኔዎችን የሚያሳልፍበት ጉባኤ መሆኑን ገልፀዋል።

ጉባኤው በዘላቂ ሰላም፣ በጸጥታ ሁኔታ፣ በኑሮ ውድነት፣ ፓርቲውን በሚያጠናክሩ ውሳኔዎች፣ እንዲሁም የፓርቲ አመራሮች የሚመረጡበትም ይሆናል፡፡ ፓርቲው ከ15 ሚሊዮን በላይ አባላት ያሉት ሲሆን፣ባለፉት ዓመታት በኢኮኖሚ፣በፖለቲካዊ፣ በማህበራዊ፣በዲፕሎማሲ፣በሰላም፣በደህንነት እና በመሰል ሃገራዊ አጀንዳዎች ላይ ስኬታማ እንደነበር ተዘግቧል፡፡ ይህ ጉባኤ የሚካሄደው በዓድዋ ድል መታሰቢያ መሆኑ ደግሞ ልዩ ትርጉም እንዳለው የስነ ልቦና ባለሙያው አቶ ማህደር ሳልህ ይናገራሉ፡፡

ከዝግጅት ክፍላችን ጋር ቆይታ ያደረጉት የስነ ልቦና ባለሙያው እንደሚሉት፣ ይህ ታላቅ ጉባኤ ዓለም አቀፍ እውቅናና ክብር ባለው የዓድዋ ድል መታሰቢያ አዳራሽ መካሄዱ ልዩ ትርጉም እንዳለው ጠቁመዋል፡፡ አክለውም፣ ጉባኤተኞቹ እንዲህ ባለው ታሪካዊና የጋራ እሴታቸው ነፀብራቅ በሆነ ስፍራ ተሰባስበው ሀሳብ መለዋወጣቸው፣ ውሳኔ ማሳለፋቸውና አቅጣጫ ይዘው መሄዳቸው የሚፈጥረው በጎ ተፅዕኖ ለሀገር ሁለንተናዊ ዕድገት የላቀ አስተዋፅኦ አለው ብለዋል፡፡

የሁላችንም ወካይ የሀገር ምልክትና ኩራት በሆነው በዚህ ስፍራ የፓርቲው ጉባኤ ሲደረግ በተሰብሳቢዎች ዘንድ የሚፈጥረው መነቃቃትና ሀገራዊ ስሜት በዚያው ልክ ከፍ ይላል፡፡ በተለይ ኢትዮጵያን እየመራ ያለውና በርካታ አባላት ያሉት ፓርቲ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ከስነ ልቦና ግንባታ አንፃር የሚፈጥረው ሀገራዊ ስሜትና መነቃቃት በቀላሉ ሊታይ የሚችል እንዳልሆነም ተናግረዋል፡፡

አባላቱ ሀገር ምን ያህል አደራ እንደጣለችባቸው፣ ኢትዮጵያ ማለት ሕብረ ብሔራዊት እና በሁሉም ዜጋ ሁለንተናዊ መስዋዕትነት የቆመችና የፀናች ሀገር መሆኗን የሚመሰክር ሕያው ስፍራ በመሆኑ አባላቱም ይህንን በሚገባ እንዲገነዘቡት፣ በዚያው ልክም ኃላፊነታቸውን በበለጠ ትጋት እንዲያከናውኑ ስንቅ እንደሚሆናቸውም የስነ ልቦና ባለሙያው ገልፀዋል፡፡

የኒዮርክ ተወላጇ ጋዜጠኛ፣ ደራሲና የስነ ልቦና ምሁር ዊኒፍሬድ ጋላገር እ.ኤ.አ በ1994 የቦታ ኃይል ወይም “ዘ ፓወር ኦፍ ፕሌስ” የተሰኘ መፅሐፍ አሳትመዋል። በዚህ መፅሐፍ አካባቢያችን ሀሳባችንን፣ ስሜታችንን እና ድርጊታችንን እንዴት እንደሚቀርጽ በስፋት ተተንትነዋል፡፡

ይህ መጽሐፍ አካባቢያችን ሀሳቦቻችንን እና ባህሪያችንን በመቅረጽ ረገድ ወሳኝ ሚና እንዴት እንደሚጫወት ያብራራል።  በተለይ ታሪካዊ ቦታዎች በፈጠራ እና በውጥረት ላይ እንዴት ተጽዕኖ እንደሚያሳድሩ ለመገንዘብ ጥሩ ምንጭ እንደሆነም ያብራራል፡፡

በመፅሐፉ እንደተገለፀው በታሪካዊ ቦታዎች ስብሰባዎችን ማካሄድ ሥነ-ልቦናዊ ጥቅሞች  አሉት፡፡ ለአብነትም በዘመናዊው ዓለም የተለያዩ ድርጅቶች ምርታማነትን ለመጨመር፣ ፈጠራን ለማዳበር እና የቡድን ስሜትን ከፍ ለማድረግ ብዙ ጊዜ በታሪካዊ ቦታዎች ላይ ስብሰባዎችን ያደርጋሉ፡፡ በዚህም በርካቶች እንደተጠቀሙበት በመፅሐፉ የተገለፀ ሲሆን፣ ከተለመደው የቢሮ አሠራር ወጥቶ በታሪክና በቁም ነገር የተሞላ ቦታ ውስጥ መግባቱ ጥልቅ ሥነ ልቦናዊ ጠቀሜታ እንዳለውም በመፅሐፉ ተመላክቷል፡፡

በሌላ በኩልም የተሻሻለ ፈጠራ እና መነሳሳት ለማምጣት እንደሚረዳ የተመላከተ ሲሆን፣ ታሪካዊ ቦታዎች ካላቸው የገዘፈ ክብርና ዝና አንፃር በዙሪያቸው ላሉ ሰዎች ለፈጠራ እንዲነሳሱ የልቦናን በር እስከመክፈት የደረሰ አበርክቶ አላቸው፡፡ ሰዎች ጥልቅ ትርጉም በሚሰጡ አካባቢዎች ሲሰበሰቡ አዳዲስ ሀሳቦችን የመፍጠር አቅማቸው ይጎለብታል፡፡ ቃል ኪዳናቸውን እንዲያፀኑና እንዲተገብሩም መነቃቃትን ይፈጥራል፡፡

በታሪካዊ ስፍራዎች ስብሰባዎችን ማድረግ ተሳታፊዎች እርስ በርሳቸው እንዲተዋወቁ ብቻ ሳይሆን ታሪካዊ  ስፍራዎች ግለሰቦች የትልቅ ታሪክ አካል መሆናቸውን እንዲያስታውሱ፣ ትልቅ በሆነ ጉዳይ ላይ አስተዋፅዖ እያደረጉ እንደሆነ እንዲገነዘቡ እና ሞራላቸው ከፍ እንዲል ብሎም ኃላፊነትን በሚገባ እንዲወጡ የማስቻል ኃይል አላቸው፡፡

እንደ መፅሐፉ ከሆነ በታሪካዊ ቦታ ላይ መገናኘት መደበኛ መሰናክሎችን በፅናትና በትብብር አልፎ ከፍ ከፍ ያሉና ሁሉን አሻጋሪ የሆኑ ድሎችን ለማስመዝገብ ይረዳል፡፡ በቡድን አባላት መካከልም የበለጠ መቀራረብ ለመፍጠር ጥሩ መንገድ ሊሆን ይችላል። ልዩ በሆነ ቦታ ላይ መሆን በራሱ የጋራ ልምድ፣ የጋራ ታሪክ እና የጋራ ግንዛቤን ይፈጥራል። ስለዚህ ታሪካዊ ቦታዎች ብዙውን ጊዜ የአመለካከት እና የማሰላሰል ስሜትን የማጋባት ባህሪ እንዳላቸው በመፅሐፉ የተገለፀ ሲሆን፣ በተለይም ታሪክ በተገለጠበት ቦታ ላይ የመሆን ልምድ በረጅም ጊዜ ግቦች፣ ራዕይ እና ትሩፋት ላይ ማሰላሰልን  እንደሚያበረታታ በመፅሐፉ ተመላክቷል፡፡

የፖለቲካል ሳይንስ ምሁሩ አቶ መሀመድ በሽር በበኩላቸው የዓድዋ ድል ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ለዓለም ህዝቦች ሁሉ ትልቅ ትምህርትን የሰጠ፣ ለበርካቶችም ነፃነትን ያስጠበቀ የተዛባውን የፖለቲካ አመለካከት ስርዓት ይይዝ ዘንድ ተምሳሌት የሆነ ድል ነው። መታሰቢያው ደግሞ ይህንን ገናና ድል በክብሩ ልክ የሚዘክር ነው፡፡ በመሆኑም በዚህ ስፍራ የሀገርን መንገድ የሚያቀና ስብሰባ ማድረግ ይቅርና በግልም ቢሆን መገኘት የሚኖረው ስነ ልቦናዊ ፋይዳ ከፍ ያለ ነው፡፡

በሌላ በኩል ደግሞ ኢትዮጵያን ዋጋ እያስከፈሏት ካሉ ችግሮች እንደ አንድ መንስኤ ይጠቀስ የነበረው የፖለቲካ ስብራት በሰላማዊና ሁሉንም አካታች በሆነ መንገድ ለውጡን  በሚመራው ፓርቲ ከለውጡ ማግስት ጀምሮ ይህን ችግር ለመቀልበስ ጥረቶች ተደርገዋል። ይህንንም ተከትሎ የተለያዩና በውጤት የታጀቡ ሀገራዊ ለውጦችንም እየተመለከትን ነው፡፡ በዚያ ላይ ፓርቲው ከ15 ሚሊዮን በላይ አባላት ያሉትና ሀገር እየመራ ያለ በመሆኑ ጉባኤውን በታላቁ እና በታሪካዊው የዓድዋ ድል መታሰቢያ ማድረጉ የሚኖረው ትርጉም በቀላሉ የሚታይ አይደለም ብለዋል፡፡

በመለሰ ተሰጋ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review