ኪነ ጥበብ የሰው ልጅ ዘወትራዊ ህይወትን ለመግለጽ እና ለሌሎች ለማካፈል ተመራጭ መንገድ ነው። በተለይም ሙዚቃን፣ ሥዕልን፣ ቅርጻ ቅርጽን፣ ፊልምን እና ቴአትርን በመጠቀም ሀሳብን፣ ስሜትን እና ታሪክን ፈጠራ በታከለበት መንገድ ለመግለጽ የሚያስችል ትልቅ አቅም አለው፡፡ በዚህም ኪነ ጥበብ የሰው ልጅ ታሪክ ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ ዛሬም ድረስ ተወዳጅነቱና ተመራጭነቱ ቀጥሏል፡፡ ከጥንታዊ እስከ ዘመናዊ ዲጂታል ስራዎች ድረስ ኪነ ጥበብ የሰው ልጅ ማንነት፣ ባህል እና ማህበራዊ ለውጥን ለመግለጽ አስተዋጽኦ አድርጓል።
ኪነ ጥበብ ማንነት፣ ባህል፣ እድገት እና ለውጥን የሚያሳይ እንዲሁም የሚያንጸባርቅ ሁነኛ መሳሪያ ነው። የተለያዩ የማህበረሰብ ክፍሎች ባህላቸውን፣ እምነታቸውን እና ታሪካቸውን በስዕል፣ በሙዚቃ እና በሌሎች የኪነ ጥበብ መንገዶች እያስተላለፉ ዛሬ ላይ የደረሱትም በዚሁ ምክንያት ነው፡፡
በተጨማሪም ኪነ ጥበብ በቃል የማይገለጽን ስሜት ለመግለጽ የሚያስችል አስተማሪ መንገድ ነው። ሰዎች የሚሰማቸውን ደስታ፣ ሃዘን፣ ቁጣ ወይም ፍርሃት በስዕል ወይም በሌሎች የኪነ ጥበብ መልኮች ማሳየት ይችላሉ።
ኪነ ጥበብ ቋንቋን እና ባህልን የሚሻገር አስተማሪ መሣሪያ ነው። በተለይም አብሮነትን በማጉላት የሰዎችን መረዳዳት እና ትብብር ያጠናክራል።
ኪነ ጥበብ ለማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ እድገት በጣም አስፈላጊ ነው። ለአብሮነት፣ ለግንኙነት እና ለተሻለ የህብረተሰብ እድገት መሰረታዊ ነው። ምክንያቱም ኪነ ጥበብ የአንድ ህዝብ እሴቶች፣ ስነ- ልቦና፣ ቋንቋ እና ልማዶች ስብስብ ነው። ይህ ሁሉ ደግሞ የህብረተሰቡን ማንነት ያጠናክራል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ኪነ ጥበብ በቱሪዝም፣ በስነ- ጥበብ፣ በሙዚቃ፣ በፊልም እና በሌሎች የፈጠራ ኢንዱስትሪዎች በኩል ኢኮኖሚያዊ እድገትን ያመጣል፡፡ ኪነ ጥበብ ሰዎችን እንዲያስቡ እና እንዲፈጥሩ ያበረታታል። ይህም በሳይንስ፣ በቴክኖሎጂ፣ በስነ-ጥበብ እና በሌሎች ዘርፎች ላይ አዳዲስ ሀሳቦችን እና መፍትሄዎችን ለማግኘት ያግዛል፡፡
ይህን የተረዱ ሀገራት ለኪነ ጥበብ ዘርፉ ልዩ ትኩረት ሰጥተው ሰርተዋል፤ እየሰሩም ነው፡፡ በሀገራችን በተለይ በአዲስ አበባ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ለኪነ ጥበብ እድገት መሰረት የሚሆኑ ስራዎች ተሰርተዋል፤ ይላል አርቲስት መምህሩ ጫሞ ለዝግጅት ክፍላችን በሰጠው አስተያየት፡፡
ለአብነትም በዓድዋ ድል መታሰቢያ የሚገኘውን አንፊ ቴአትር መጥቀስ ይቻላል፡፡ እንጦጦ የሥነ ጥበብ ማዕከልም ሌላኛው ተጠቃሽ ነው፡፡ በሳይንስ ሙዚዬም አጠገብ በጉልላት (ዶም) የተሠራ የአምፊ ቴአትር ማሳያም ተገንብቷል፡፡ በመዲናዋ በኮሪደር ልማቱ በተሰሩ የተለያዩ የመዝናኛ ቦታዎች ላይ የተለያዩ የሙዚቃ ድግሶችና የኪነ ጥበብ መሰናዶዎችን ማየትም የተለመደ ሆኗል። በተጨማሪም በኮሪደር ልማቱ የተዋቡ ስፍራዎች የሰርግ ፎቶ እና ቪዲዮዎች፣ ፊልሞች፣ የሙዚቃ ክሊፖች በሚሰሩ ባለሙያዎች ተመራጭ ሆነዋል፡፡
የኪነ ጥበብ ዘርፉን ለማሳደግ በፕሮጀክቶች ግንባታ የኪነ ጥበብ ማዕከላት መገንባታቸው አስፈላጊ ነው፡፡ እነዚህ ማዕከላት ስራዎቹን ለማስተባበር፣ ለማስተዳደር፤ ለህዝብ ለማቅረብ እና የጥበብ እድገትን ለማስፋፋት የሚያስችሉ መሠረታዊ ለውጦች ናቸው።
አርቲስት መምህሩ ጫሞ ከላይ ከተጠቀሰው በተጨማሪ የኪነ ጥበብ ማዕከላት ልማትን ለማፋጠን፣ የጋራ መግባባት እና አብሮነት እንዲጠናከር ያግዛሉ። እነዚህ ማዕከላት ለልዩ ልዩ የኪነ ጥበብ ሥልጠናዎች እድል በመፍጠር አዳዲስ የኪነ ጥበብ ባለሙያዎች ማፍራት ይችላሉ። የልምድ ልውውጥን ለማሳደግም ሁነኛ ፕሮጀክቶች ናቸው፡፡
በተጨማሪም የኪነ ጥበብ ማዕከላት ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎችን እና መሳሪያዎችን በመጠቀም የኪነ ጥበብ ስራዎችን ለማሻሻል ያስችላሉ። ለአብነትም የዓድዋ ድል መታሰቢያ የዓድዋን ድል የሚመጥን ትልቅ አሻራ ከመሆኑ በተጨማሪ የዘመናችን የመጨረሻ ቴክኖሎጂ ወዳ ሀገራችን ያመጣ ነው። በመታሰቢያው የሚገኘው ሙዚየም ባለ ሦስት አቅጣጫዊ (3D) ትንበያ ሆሎግራም ቴክኖሎጂ (Hologram Technology) የተገጠመለት ነው። ሆሎግራም ቴክኖሎጂ እንደ ካሜራ ወይም መነጽር ያሉ ልዩ መሳሪያዎችን ሳይጠቀም ምስሉ ከየትኛውም ማዕዘን በመቅረፅ ዳታ የሚያከማች ቴክኖሎጂ ነው።
ከሆሎግራም ገጸ-በረከቶች አንዱ በመዝናኛ ኢንዱስትሪ ውስጥ ያለው አስተዋጽኦ ነው፡፡ ቴክኖሎጂው ከመፈጠሩ ጀምሮ በህይወት የሌሉ ተዋናዮችና አርቲስቶች በህይወት ከሚገኙ የኪነ ጥበብ ሰዎች ጋር በመድረክ ላይ ስራቸውን እንዲያቀርቡ አስችሏል፡፡ ለምሳሌ፡- ታዋቂው አቀንቃኝ ማይክል ጃክሰን በጎርጎሮሳውያን የዘመን ቀመር 2014 የቢልቦርድ ሙዚቃ ሽልማት ወቅት በሆሎግራም የተለያዩ ስራዎች ያቀረበ ሲሆን፤ በበርካቶች ዘንድ በህይወት የተመለሰ እስኪመስል ድረስ ግርምትን ፈጥሯል፡፡
በተጨማሪም ሆሎግራም በፊልሞች እና በቪዲዮ ስራዎች ሂደት ውስጥ አስደናቂ የእይታ ምስሎችን ለመፍጠር ጥቅም ላይ ይውላል፡፡ ይህም ለተመልካቾች በእውነታ እና በልብ ወለድ መካከል ያለውን መስመር የሚያደበዝዝ መሳጭ ክስተትን ፈጥሯል፡፡ እነዚህ እድገቶች የመዝናኛ ዘርፉን መልክ እና ቀጣይ መንገድ ቀይረዋል፡፡ በቅርብ ዓመታት ውስጥ የዚህ ቴክኖሎጂ ውጤት በመድረክ፣ በፊልም፣ በቴአትር እና በሙዚቃ ድግሶች ጥቅም ላይ ውሏል።
ይህ ቴክኖሎጂ በሀገራችን ለመጀመሪያ ጊዜ በዓድዋ ድል መታሰቢያ ምርቃት መርሃ ግብር ላይ ተሞክሮ ውጤታማ መሆኑ ይታወሳል፡፡ ይህም ባለፉት ዓመታት የኪነ ጥበብ ዘርፉን በቴክኖሎጂ እና በሌሎች ዘርፎች ለማሳደግ ከተሰሩት ስራዎች ውስጥ ተጠቃሽ ነው፡፡
ከምርቃቱ እለት አንስቶ በዓድዋ ድል መታሰቢያ ውስጥ የተሰራው አንፊ ቴአትር በርካታ ኪነ ጥበባዊ ሁነቶችንም ለማስተናገድ በቅቷል፡፡ “አስቴር” የተሰኘው የመጀመሪያው ባለ ቀለም ፊልም ዲጅታላይዝድ በሆነ መንገድ ተሰርቶ በቅርቡ የተመረቀው በዚሁ ቴአትር ቤት ውስጥ ነው፡፡
ፊልሙ የተመረቀው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አቤቤን ጨምሮ አንጋፋ የኪነ-ጥበብ ባለሙያዎችና ተጋባዥ እንግዶች በተገኙበተ ነው፡፡ ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ኪነ ጥበብ የሀገራችንን የልዕልና ጉዞ እንዲያሳልጥ አስፈላጊ መሰረተ ልማቶችን ገንብቶ ለሕዝብ ጥቅም አቅርቧል፡፡ ዘርፉን ይበልጥ የማስፋፋቱን ስራ አጠናክረን የምናስቀጥል ይሆናል ሲሉም ከንቲባዋ የፊልም ምርቃቱን አስመልክተው በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት ጽሑፍ ጠቅሰዋል፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ባሕል ኪነ ጥበብና ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊ ሂሩት ካሣው (ዶ/ር) በቅርቡ በመዲናዋ በተደረገ የኪነ ጥበብ ዝግጅት ላይ ባደረጉት ንግግር፣ ኪነ ጥበብ አብሮነትን፣ ወንድማማችነትና እህትማማችነትን እንዲሁም በጋራ የማደግን እሳቤ በማስረጽ ሚናው ከፍተኛ መሆኑን አንስተው፤ በዚህም በሁሉም በከተማዋ የሚገኙ ክፍለ ከተሞች ወርሃዊ የኪነ ጥበብ ምሽት እየተካሄደ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡
ቢሮ ኃላፊዋ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከተማዋን የብልጽግና ተምሳሌት ለማድረግ እያከናወናቸው ያሉ ፕሮጀክቶች ኪነ ጥበብን ለማሳደግ የሚያስችሉ መሠረተ ልማቶችንም ያካተቱ መሆናቸውን በመግለጽ እነዚህን ስኬታማ ሥራዎችና የብልጽግና ጉዞን በኪነ ጥበባዊ ሁነቶች የማንጸባረቅና የማስተዋወቅ እንቅስቃሴው ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባ አክለው ገልጸው ነበር። በሁሉም ክፍለ ከተሞች ኪነ ጥበባዊ ዝግጅቶች እየተካሄዱ ሲሆን መርሃ ግብሮቹ የሚከናወኑት በኮሪደር ልማቶቹ በተሰሩ የመዝናኛ ስፍራዎች ነው፡፡ ይህም ባለፉት ዓመታት በመዲናዋ ለኪነ ጥበብ የተሰጠውን ትኩረት ያሳያል፡፡ በትልልቅ ፕሮጀክቶች ከተካተቱ የኪነ ጥበብ ማዕከላት በተጨማሪ በእነዚህ የህዝብ መናፈሻ ቦታዎች ግጥም፣ ጭውውት፣ ባሕላዊና ዘመናዊ ሙዚቃዎች እንዲሁም የሰርከስ ዝግጅቶች ለታዳሚያን መቅረባቸውን ቀጥለዋል፡፡
አርቲስት መምህሩ ባለፉት ዓመታት የኪነ ጥበብ ዘርፉን ለማሳደግ የተለያዩ ስራዎች ተሰርተዋል፡፡ ነገር ግን ኪነ ጥበብ ለአንድ ሀገር እድገት ካለው ዋጋ አንጻር ብዙ የሚቀሩ ነገሮች አሉ፡፡ አደረጃጀትን ጨምሮ ሌሎች ሁኔታዎች ኪነ ጥበቡ በሚፈለገው ልክ ወደፊት እንዳይራመድ አድርጓል ሲል በማጠቃለያ ሃሳቡ አንስቷል፡፡
በአጠቃላይ ኪነ ጥበብ የሰው ልጅን ሕይወት ለማሻሻል፣ ለለውጥ እና ለልማት ለማነሳሳት ከፍተኛ ሚና ይጫወታል። ኪነ ጥበብን ለማሳደግ በትኩረት መስራት ያስፈልጋል የሚባለውም ለዚሁ ነው። ባለፉት ዓመታት በሀገራችን በተሰሩ ልማቶች ውስጥ የጥበብ ማዕከላት መገንባታቸው ጠቀሜታው የጎላ ነው፡፡ ከዚህ ጎን ለጎን ኪነ ጥበብን በትምህርት ስርዓት ውስጥ በማካተት፣ የኪነ ጥበብ ተቋማትን በገንዘብ፣ በቁሳቁስ እና በሰው ኃይል በማጠናከር እና በማዕከላቱ ውስጥ የኪነ ጥበብ አውደ ርዕዮችን በየጊዜው በማዘጋጀት ዘርፉን የበለጠ ማሳደግ ያስፈልጋል፡፡
በጊዜው አማረ