AMN – የካቲት 2/2017 ዓ.ም
ብሔራዊ መግባባትን ለማጎልበት የተጀመሩ ተግባራት ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግስት ዋና ተጠሪ ሚኒስትር ተስፋዬ ቤልጂጌ(ዶ/ር) ገለጹ።
ብልፅግና ፓርቲ ባካሄደው ሁለተኛው መደበኛ ጉባኤ በተለያዩ መስኮች የተገኙ ውጤቶችን የሚያስቀጥሉ ውሳኔዎች አስተላልፏል።
የብልጽግና ፓርቲ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባልና በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግስት ዋና ተጠሪ ሚኒስትር ተስፋዬ ቤልጂጌ(ዶ/ር) ፓርቲው ባሳለፋቸው ውሳኔዎች ዙሪያ በሰጡት ማብራሪያ ሀገራዊ መግባባትን እውን ለማድረግ የተጀመሩ ተግባራት ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ አብራርተዋል።
ለስኬታማነቱም የጋራ ገዥ ትርክትና አገራዊ ሥነ ልቦናን ይበልጥ ማዳበር ላይ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
ለአብነትም ለውጡን ተከትሎ ለበርካታ ችግሮች መንስኤ የሆነውን ነጠላ ትርክት በአገራዊ አሰባሳቢ ትርክት ለማረም መሰራቱንም አንስተዋል።
ፖለቲካው ከነበረበት ጽንፍ ተላቆ የመሃል ፖለቲካ እሳቤ ቦታ እንዲይዝ መደረጉ ለብሄራዊ መግባባት መሰረት መጣሉን ጠቁመው፤ በዚህም ውጤት መምጣቱን በብልጽግና ፓርቲ ሁለተኛ መደበኛ ጉባኤ ላይ መገምገሙን አክለዋል።
በቀጣይም በብሄራዊ መግባባት ዙሪያ የሚከናወኑ ሥራዎች በተጠናከረ መልኩ ገቢራዊ እንዲሆኑ አቅጣጫ መቀመጡን ተናግረዋል።
ሀገራዊ መግባባቱ ለሁሉም የምትሆን ኢትዮጵያን መገንባትን በማለሙ ለውጤታማነቱ የሁሉም ዜጋ ተሳትፎ አስፈላጊ ነው ብለዋል።
ለዚህም ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን የተቋቋመበት ዓላማ ግቡን እንዲመታ ብልጽግና ፓርቲ እንደ አንድ ባለድርሻ አካል የሚጠበቅበትን ሚና እንደሚወጣም አረጋግጠዋል።
በጋራ ትርክቱ መሰረታዊ ተቃርኖዎች ተፈትተው ዘላቂ ሠላም እንዲሰፍን እየተከናወኑ ያሉ ተግባራት ተጠናክረው እንደሚቀጥሉም ተናግረዋል።
በሌላ በኩል ነጻና ገለልተኛ ተቋማት መኖራቸው ለጠንካራ ሀገር ግንባታ ቁልፍ ጉዳይ መሆኑን የተናገሩት ተስፋዬ ቤልጅጌ(ዶ/ር)፤ በዚህ ረገድ ባለፉት የለውጥ ዓመታት ነጻና ገለልተኛ ተቋማትን ማንበር ላይ አበረታች ጅምሮች መኖራቸውን ጠቅሰዋል።
በሀገር ጉዳይ ላይ በጋራ መሥራት አለብን ያሉት ሚኒስትሩ ህዝቡ፣ ፖለቲከኞች፣ መገናኛ ብዙሃን፣ ዳያስፖራውና ሊሎችም በትጋት መሳተፍ እንዳለባቸው አመላክተዋል።
ኃይልን የመፍትሄ አማራጭ ከማድረግ ይልቅ ለሠላማዊ መንገዶች ቅድሚያ በመስጠት በሰለጠነ መንገድ ተወያይቶ ለችግሮች እልባት የመስጠት ባህል መጎልበት እንዳለበትም አጽንኦት መስጠታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።