AMN – የካቲት 2/2017 ዓ.ም
ድህነት እና ኋላቀርነትን በዘላቂነት መፍታት የሚቻለው ያሁኑን ብቻ ሳይሆን ቀጣዩን ትውልድ ማዕከል ያደረገ ስራ መስራት ሲቻል ነው ሲሉ የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት ፕሬዚዳንት አቶ ሽመልስ አብዲሳ ገለጹ፡፡
የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት ፕሬዚዳንት አቶ ሽመልስ አብዲሳ ከጨፌ ኦሮሚያ አባላት ለተነሱላቸው ጥያቄዎች ምላሽና ማብራሪያ እየሰጡ ነው።
ተፈላጊውን ልማት እና ዕድገት ማምጣት የሚቻለው ገቢ መሰብሰብ ላይ ስኬታማ ስራ ማከናወን ሲቻል ነው ያሉት አቶ ሽመልስ ገቢ እንደ ጤና ፣ ትምህርት እና የመሳሰሉትን መሰረታዊ አገልግሎቶች ለሕዝብ ተደራሽ ለማድረግ አስፈላጊ ነው በመሆኑም አሰባሰቡ ላይ በትኩረት መስራት ያስፈልጋል ብለዋል።
ገቢ ያለ ደረሰኝ የሚሰበስብ አካል ካለ እሱ የሕዝብ ጠላት ነውም ብለዋል።
ድህነትን ለማሸነፍ ትውልዱን የተለያዩ የሙያ ባለቤት ለማድረግ መስራት ይጠይቃል ያሉት አቶ ሽመልስ እዚህ ላይም በልዩ ትኩረት መስራት አለብን ብለዋል።
በኦሮሚያ ክልል በሕዝብ እና በመንግስት የተቀናጀ ስራ በርካታ የልማት ስራዎች ላይ አስደናቂ ስኬት ተገኝቷል ያሉት ፕሬዝደንቱ ለምሳሌ ቡራ ቦሩ ላይ የተገኘውን ውጤት እንደ ማሳየት መውስድ ይቻላል ብለዋል።
ቀን እና ሌሊት የመስራት ባህል ላይ ጥሩ ጅምር በመኖሩ አሁንም ቢሆን ጠንክሮ መስራት ይጠይቃል ብለዋል፡፡
የመንግስት የስራ ባህል መሻሻል እንዳለበት ያመለከቱት አቶ ሽመልስ አሁን ባለው አካሄድ ድህነትን ማሸነፍ አይቻልም ብለዋል።
ድህነት እና ኃላቀርነትን ከሀገራችን ከስር መሰረቱ ለመንቀል ምኞት ብቻ ሳይሆን ቀጣይነት ያለው ስራ መሰራት ይጠይቃል ብለዋል።
በዳንኤል መላኩ