AMN – የካቲት 3/2017 ዓ.ም
በመዲናዋ የጣራ እና ግድግዳ ግብር የመክፈያ ጊዜ እየተጠናቀቀ በመሆኑ ግብር ያልከፈሉ ነዋሪዎች እንዲከፍሉ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ገቢዎች አሳስቧል፡፡
በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ቻርተር ቁጥር 361/1995 አንቀጽ 52 ንዕስ አንቀጽ 6 መሰረት የከተማ ቦታ ኪራይ እና የቤት ግብር የመወሰን እና የመሰብሰብ የህግ ስልጣን ለከተማ አስተዳደሩ የተሰጠ መሆኑ ይታወቃል፡፡
በመሆኑም በተለመዶ የጣራና ግድግዳ ግብር እየተባለ የሚጠራው የቤትና ቦታ ግብር የሚከፍሉ ግብር ከፋዮች ግብሩ ያለቅጣትና ወለድ የሚከፈልበት ጊዜ እየተጠናቀቀ በመሆኑ ያልከፈሉ ነዋሪዎች እንዲከፍሉ አሳስቧል፡፡
በከተማዋ 429 ሺህ 829 ግብር ከፋዮች የቤትና ቦታ ግብር ክፍያ እንዲፈፅሙ የሚጠበቁ ሲሆን፣ እስከ አሁን አብዛኛው ግብር ከፋዮች የቤትና ቦታ ግብር መፈፀማቸው ተገልጿል፡፡
ስለሆነም ያልከፈሉ ባለይዞታዎች የሚጠበቅባቸውን ግብር ከየካቲት ወር አጋማሽ ጀምሮ ከሚከሰት መጨናነቅ እና ቅጣት ለመዳን በቀሩት ቀናት ግዴታቸውን በመወጣት ለከተማው ልማት የድርሻቸውን እንዲወጡ ቢሮው ለአዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ በላከው መግለጫ አሳስቧል፡፡