AMN – የካቲት 4/2017 ዓ.ም
የአዲስ አበባ ከተማ የዘንድሮውን የአፍሪካ ህብረት ጉባኤ ለማስተናገድ ከመቼውም ጊዜ በላይ ዝግጅት ማድረጓን የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ፡፡
ከንቲባ አዳነች ይህን ያሉት እጅግ ውብ በሆነ እና በዘመናዊ መልኩ ተገንብቶ ለአገልግሎት ዝግጁ በሆነው የአዲስ ኢንተርናሽናል ኤግዚብሽን እና ኮንቬንሽን ማዕከል ተገኝተው በሰጡት ማብራሪያ ነው፡፡
አዲስ አበባ ከተማ የአፍሪካ የፖለቲካ ካፒታል እና ሶስተኛዋ የዲፕሎማቲክ ከተማ እንደመሆንዋ መጠን፣ ባለፈው አመት የአፍሪካ ህብረት ጉባኤን ስናስተናግድ የከተማችንን ደረጃ የማይመጥኑ ነገሮች ለመደበቅ የተለያዩ ዘዴዎችን ተጠቅመን ነበር ያሉት ከንቲባ አዳነች፣ በዚህ አመት ግን መዲናዋ ከመቼውም ጊዜ በላይ አምራና ደምቃ ጉባኤውን ለማስተናገድ ዝግጁ ሆናለች ብለዋል፡፡
የአዲስ አበባ ህዝብም ለጉባኤው መሳካት የበኩሉን አስተዋጽኦ ለማድረግ ዝግጅት ማድረጉንና በመዲናዋ ውስጥ የሚገኙ ሆቴሎችም ለጉባኤው የሚመጡ እንግዶችን ለመቀበል ዝግጅት አድርገዋል ብለዋል፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ የአፍሪካ ህብረት ጉባኤን ብቻ ሳይሆን ማናቸውንም ዓለም አቀፍ የሆኑ ጉባኤዎችን፣ ኮንፍረንሶች እና ኤግዚብሽኖችን ለማስተናገድ የሚያስችል አቅምና ግብዓቶችን እያሟላች ትገኛለች ብለዋል ከንቲባ አዳነች፡፡
ከንቲባዋ አያይዘውም ለዚህ ማሳያ የሚሆነው ደግሞ ግንባታው ተጠናቆ ለአገልግሎት ዝግጁ የሆነው የአዲስ ኢንተርናሽናል ኤግዚብሽን እና ኮንቬንሽን ማዕከል አንዱ ማሳያ ነው ብለዋል፡፡

“ባለፈው አመት የአድዋ ድል መታሰቢያን መርቀን ለአፍሪካ ህብረት ጉባኤ አንዳንድ ሁነቶችን ለማስተናግድ የሚያስችል አዲስ ብስራት ይዘን እንደቀረብነው ሁሉ፣ ዘንድሮ ደግሞ በአርባ ሄክታር የመሬት ስፋት ላይ ያረፈውን እና ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀውን የኤግዚብሽንና ኮንቬንሽን ማዕከል እነሆ ብለናል” ነው ያሉት ከንቲባ አዳነች አቤቤ፡፡
ይህ ማዕከል በአንድ ጊዜ ከ10ሺ በላይ ሰዎችን ማስተናገድ የሚችል ሲሆን ከሶስት ሺህ እስከ አራት ሺህ ሰዎችን መያዝ የሚችሉ ሁለት ትላልቅ አዳራሾች እና ከአንድ መቶ እስከ አንድ ሺህ የሚደርሱ ሰዎችን የመያዝ አቅም ያላቸው ወደ ስምንት የሚደርሱ ትናንሽ አዳራሾች እና ኤግዚብሽን የሚካሄድባቸው ቦታዎች እንዳሉትም ከንቲባ አዳነች አብራርተዋል፡፡
በተጨማሪም ማዕከሉ በአንድ ጊዜ እስከ አንድ ሺህ ሰዎችን ማስተናገድ የሚችሉ አልጋዎች ያሏቸው ሆቴሎች እና ትላልቅ ሬስቶራንቶችም እንዳሉት ገልጸዋል፡፡
ይህም በአዲስ አበባ ከተማ ደረጃ እጅግ በጣም ትልቅ የሚባል መሆኑ የገለጹ ሲሆን ለዘንድሮው የአፍሪካ ህብረት ጉባኤ ይዘነው የቀረብን አዲስ ነገር ለሀገራችን ብቻ ሳይሆን ለአፍሪካም ኩራት ነው ብለዋል፡፡
ማዕከሉ፣ ለአዲስ አበባ ብቻ ሳይሆን ለአፍሪካዊያ ወንድም እህቶች ሁሉ ኤግዚብሽኖችን፣ ኮንፍረንሶች እና የተለያዩ ዓለም አቀፍ ሁነቶችን ለማካሄድ የሚያስችል እንደሆነም ነው ከንቲባዋ የተናገሩት፡፡
ማዕከሉ፣ ዘጠና በመቶው በከተማ አስተዳደሩ ወጪ እና ቀሪው ደግሞ ሌሎች አካላትን በማሳተፍ እንደተገነባ የገለጹት ከንቲባ አዳነች አቤቤ፣ ለፕሮጀክቱ መሳካትም እንኳን ደስ ያለን ብለዋል፡፡
በአስማረ መኮንን