AMN – የካቲት 5/2017 ዓ.ም
የኬንያንና ኢትዮጵያን ሁለንተናዊ ትብብር ይበልጥ በሚያጠናክሩ ተግባራት ላይ አተኩረን እንሰራለን ሲሉ የኬንያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር እና የካቢኔ ጉዳዮች ኃላፊ ሙሳሊያ ሙዳቫዲ ገለጹ።
የኬንያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር እና የካቢኔ ጉዳዮች ኃላፊ ሙሳሊያ ሙዳቫዲ በ46ኛው የአፍሪካ ሕብረት የስራ አስፈፃሚዎች ምክር ቤት ስብሰባ ላይ እየተሳተፉ ነው።
የኬንያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር እና የካቢኔ ጉዳዮች ኃላፊ ሙሳሊያ ሙዳቫዲ እንደገለጹት፥ኢትዮጵያ እና ኬንያ በጸጥታ፣ በንግድ እና በህዝብ ለህዝብ ግንኙነት ጠንካራ ትስስር አላቸው።
ለአብነት በሁለቱ ሀገራት ድንበር በኩል በሰላምና ጸጥታ ጉዳዮች ላይ በጋራ እንደሚሰሩ ጠቅሰዋል።
ከዚህም ባለፈ በአፍሪካ አህጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጣና ማዕቀፍ በኩል በንግድና ኢንቨስትመንት ዘርፎች ትብብራቸው ይበልጥ ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ ገልጸዋል።
ሙሳሊያ ሙዳቫዲ አክለውም፥ ለአህጉሪቱ ሰላምና መረጋጋት ብዙ መስራት እንደሚያስፈልግ ገልጸው፥ ከዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ጋርም በትብብር መስራት ያስፈልጋል ብለዋል።
የጸጥታና ደህንነት ጉዳይ በአንድ ሌሊት የሚፈታ አለመሆኑን ጠቅሰው፥ የጸጥታ ችግር ያጋጠማቸውን ሀገራት ወደተሟላ ሰላም ለመመለስ ከባለድርሻ ሀገራት ጋር በመተባበር ውይይቶችን አጠናክሮ መቀጠል አስፈላጊ መሆኑን መናገራቸውን ኢዜአ ዘግቧል።