ኢትዮጵያ ባለፉት አምስት ዓመታት አስደናቂ ለውጥ አስመዝግባለች- ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)

You are currently viewing ኢትዮጵያ ባለፉት አምስት ዓመታት አስደናቂ ለውጥ አስመዝግባለች- ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)

AMN – የካቲት 8/2017 ዓ.ም

ኢትዮጵያ የተለያዩ ፈታኝ ሸክሞች ቢኖሩባትም ፈተናዎችን በመጋፈጥ በቁርጠኝነት ወደ ፊት በመራመድ ባለፉት አምስት ዓመታት አስደናቂ ለውጥ አስመዝግባለች ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ተናግረዋል፡፡

38ኛው የአፍሪካ ሕብረት የመሪዎች ጉባኤ መካሄድ ጀምሯል።

በጉባኤው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ባደረጉት ንግግር፣ ውስብስብ እና በየጊዜው የሚለዋወጠውን ቀጣናዊ እና ዓለም አቀፋዊ ውጣ ውረድ አስሰናል ብለዋል።

ሆኖም፣ በጽናት እና በትብብር፣ የጋራ ብልጽግና እና ራዕያችን ለማረጋገጥ እንቀጥላለን ሲሉም ተናግረዋል፡፡

ስኬቶቻችን በራሳቸው ይናገራሉ ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ የሀገርን ብዝሃነት በሚያረጋግጥ መልኩ የፕሮቶኮል ስርዓቱ ተሻሽሎ ወደ አካታች፣ የመድበለ ፓርቲ ማዕቀፍ ተቀይሯል ብለዋል፡፡

እነዚህን ማሻሻያዎች ለማጠናከር እና አንድነትን፣ ዕርቅን እና ሰላምን ለመፍጠር ብሔራዊ ምክክር ላይ እየተሰራ እንደሆነም ገልጸዋል።

በኢኮኖሚው ዘርፍም ጠንካራ እና የማይናወጥ ኢኮኖሚ መገንባቱን ጠቁመዋል።

ባለፉት አምስት ዓመታት መልማት የሚችለውን መሬት በእጥፍ በማሳደግ የሰብል ምርትን ወደ 700 ሚሊዮን ኩንታል ማሳደግ እንደተቻለ እና ከዚህ ውስጥም ስንዴ 40 በመቶውን እንደሚይዝ ገልጸዋል።

በዚህም ዛሬ ላይ ኢትዮጵያ ከአፍሪካ ቀዳሚዋ ስንዴ አምራች ሀገር ሆናለች በማለት ተናግረዋል።

በጋራ ጥረት በተሰራው ሥራም በአምስት ዓመታት ውስጥ የውጭ ብድርን ከ50 በመቶ በላይ በመቀነስ እና የውስጥ ገቢን በማሳደግ የ8.1 በመቶ እድገት ማስመዝገብ መቻሉን ጠቁመዋል፡፡

በትምህርት ዘርፍም 40 ሺህ የሚሆኑ የመዋዕለ ሕጻናት እና የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤቶች እንደተገነቡ እና የትምህርት ተደራሽነትን ለማስፋፋት መሰራቱን ገልጸዋል፡፡

በታምራት ቢሻው

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review